የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር አሽ ካርተር ትላንት እሁድ ኤቢሲ (ABC) በተባለው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ሲናገሩ ዩናይትድ ስቴስከ ኢራቅና ከአስፍጋኒስታን ተመክሮ ባየችው መሰረት ለድል ወሳኝ የሚሆነው ውጊያውን ለማሸነፍ ከተቻለ በኋላ በአከባቢው ሰላም እንዲዘልቅ የማድረግ ብቃት ያላቸው የአከባቢ ሀይሎች መኖር ነው ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት ኢራቅና ሶርያ ላይ እንዲህ አይነት ቡድኖችን ማግኘት ከባድ ነው። እንዲህ አይነት ሃይሎችን ለማግኘት፣ ለማዳበርና ለማበረታት ጊዜ የሚወስደውም ለዚህ ነው። በአሁን ወቅት እስላማዊ መንግስት ነኝ የሚለውን ቡድን ለመዋጋት የሚፈልጉና በውጊያው ውጤት ያስገኙ አንዳንድ ሃይሎች አሉ። እንዲህ አይነቶቹ ሀይሎች እየተበራከቱ ከሄዱ እኛም የበለጠ ስራ እንሰራለን። ጽንፈኛውን ቡድን ለመዋጋት የሚፈልጉና ብቃት ያላቸው ቡድኖች ካሉ እኛም በበለጠ እንሰራለን። ለዘላቂ ድል ወሳኝ የሚሆነው ይህ ነው” ብለዋል።
ካርተር አያይዘውም ዋናው ነገር በጉዳዩ የሚሳተፉት የዩናትድ ስቴትስ ወታደሮች ብዛት ሳይሆን የሚሰሩት ነገር ነው ብለዋል።
“የአየር ድብደባ ለማካሄድ የሚያስችሉና መረጃ ለማቅረብ የሚረዱ ልዩ ክህሎቶች አሏቸው። ከአከባቢው ህዝብ የተሰባሰቡ ሀይሎችን ለማበራከት የሚረዱ ሃይሎች ናቸው” በማለት አስገንዝበዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የመረጃ ጉዳይ ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር ዳያን ፈይንስቴን በበኩላቸው ትላንት ኤንቢሲ (NBC) በተባለ የአሜርካ ቴሌቪዥን ቀርበው ሲናገሩ ወደ ሶርያ የሚላኩት ልዩ የዩናትድ ስቴትስ ሀይሎች ቁጥር ለተላኩበት ተልእኮ በቂ አይደለም ብለዋል።
“በፍጥነት የሚገቡና የሚወጡ የልዩ እንቅስቅሴ ሀይሎችን የምንጠቀም ከሆነ እስላማዊ መንግስት ነኝ የሚለውን ቡድን ለመምታት በሚያስችል የተሟላ መልክ መሆን ይኖርበታል። ጽንፈኛው ቡድን ራካ ወይም በሌላ ቦታ በሚገኝ አንድ ህንጻ ላይ የተወሰነ ሳይሆን በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሰፈረ ነው። ሌላው እየተሰማ ያለው አመለካከት ደግሞ በአየር ቦምብ በማወረድ ብቻ የሚፈታ ነገር አይደለም የሚለው ነው። ሰባት ሺህ ጊዜ የአየር ድብደባ ተካሂዷል። ሌሎች ወገኖችም የአየር ድብደብ አካሂደዋል። አብዛኛውን የአየር ድብደባ ያካሄድነው እኛ ነን" ሲሉም ፈይንስቴን አክለውበታል።
ሴኔተር ዳያን ፈይንስቴን አያይዘውም ሶርያ ያለውን እስላማዊ መንግስት ነኝ የሚለውን ቡድን ለማሸነፍ ከሩስያ ጋር የተባበረ ስትራቴጂ እንዲቀየስ ሃሳብ አቅርበዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት በዘገበው መሰረት ሶርያና ኢራቅ ውስጥ ጽንፈኛውን ቡድን ኢላማ በማድረግ የሚካሄደው በዩናይትድ ስቴትስ የተመራ የአየር ድብደባ እስካለፈው አርብ በነበሩት 8 ቀናት ውስጥ ተባብሶ ነበር።
የዩናይትድ ስቴትስ መከላከይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፓትሪክ ራይደር በአንድ ላይ በብዛት የሚያካሄዳቸው የአየር ድብዳባዎች በተለያዩ ግንባሮች የሚገኙትን እስላማዊ መንግስት ነኝ የሚለው ቡድን አማጽያንን እያስጨነቁ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ዘጋቢ ቪክተር ቢቲ ያጠናቀረውን ዘገባ አዳነች ፍሰሀየ አቅርባዋለ። የድምጽ ፋይሉን በመጫን ያዳምጡ።