በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ኤምባሲ ዐዲስ አበባን በቁቤ “ፊንፊኔ” ማለቱ ተቃውሞ ሲያስነሣ ያበረታቱም አሉ


የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ዐዲስ አበባ
የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ዐዲስ አበባ

በዐዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የቪዛ እና ሌሎች አገልግሎቶችን አስመልክቶ፣ ባለፈው ረቡዕ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ በአፋን ኦሮሞ ባወጣው ማስታወቂያ፣ ዐዲስ አበባ በሚለው የርእሰ መዲናዪቱ ስያሜ ፈንታ “ፊንፊኔ” የሚለውን አጠራር መጠቀሙን ተከትሎ፣ ከኢትዮጵያውያን የሲቪክ ማኅበረሰቦች የተቃውሞ፣ ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ደግሞ የድጋፍ ምላሾችን አስተናግዷል።

በዐዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾቹ ላይ፣ ኤምባሲው ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ በቁቤ ማለትም በአፋን ኦሮሞ ፊደል በተጻፈ ማስታወቂያ ላይ፣ ዐዲስ አበባን ለማመልከት “ፊንፊኔ” የሚለውን አጠራር መጠቀሙን ተከትሎ፣ የተቃውሞ እና የድጋፍ ምላሾችን አስተናግዷል።

ሃያ ሁለት የሚኾኑና በአብዛኛው ነዋሪነታቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን የሲቪክ ድርጅቶች፣ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ባለፈው ቅዳሜ በላኩት የተቃውሞ ደብዳቤ፣ “በዐዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ አጨቃጫቂ የኾነውንና በአክራሪ የኦሮሞ ቡድኖች የሚቀነቀነውን ‘ፊንፊኔ’ የሚለውን ስም በመጠቀሙ ቁጣችንን እንገልጻለን፤” ብሏል።

ደብዳቤው በይቀጥላልም፣ “ኢትዮጵያውያን፣ በብሔር ጥላቻ ላልተበከለ እውነተኛ ዴሞክራሲ በሚታገሉበት ወቅት፣ ኤምባሲው ያስተላለፈው መልዕክት፣ በኢትዮጵያውያን ክብር እና ኩራት ላይ የተቃጣ ስድብ ብቻ ሳይኾን፣ ግልጽ የኾነ የዲፕሎማሲ ሥርዓትን የጣሰ ድርጊት ነው፤” ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።

“በኢትዮጵያ አሁን እየታዩ ካሉት ችግሮች አንጻር፣ የኤምባሲው የስም አጠቃቀም፣ በማኅበረሰቦች መካከል ግጭትን የሚያበረታታና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሜሪካ ላይ ያለውን ገለልተኛ የኾነ የአስታራቂነት ሚና በተመለከተ እንዳይተማመን የሚያደርግና በአገሪቱም ኾነ በቀጣናው በሚኖረው መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያስከትል ነው፤” ሲልም አክሏል።

ኤምባሲው፣ መልዕክቱን ያስታወቀበትን የርእሰ መዲናዋን ስያሜ መልሶ እንዲስብ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅና ወደፊት “ሓላፊነት የጎደለው” ነው ያሉትን ተመሳሳይ መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብ፣ ደብዳቤው ጠይቋል።

የኢትዮጵያውያን የሲቪክ ድርጅቶቹ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የጻፉትን ደብዳቤ ተከትሎ፣ የኦሮሞ ቅርስ እና አመራር ተሟጋች ማኅበር(OLA)ን ጨምሮ 24 የሚደርሱና በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ሰኞ ዕለት ለሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ደግሞ፣ “የተጠቀሰውንና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ኤምባሲው ዒላማ መደረጉ፣ ራሳቸውን በኢትዮጵያ ስም ያሰባሰቡ አክራሪ ቡድኖች፣ በኦሮሞዎች ላይ የሚያስተላልፉትን የፈጠራ ትርክትን የሚያሳይ ነው፤” ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ሲቪክ ድርጅቶቹ፣ ደብዳቤውን ያስገቡት፥ ለአንድ ሳምንት ያህል፣ በኤምባሲው እና በኢትዮጵያ ዐዲስ በተሾሙት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ ላይ፣ ዘመቻ መደረጉን ተከትሎ እንደኾነ፣ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ደርጅቶቹ ደብዳቤ አመልክቷል።

የኦሮሞ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው፣ “ለዐሥርት ዓመታት እነዚኽ ቡድኖች፣ በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ብሔሮችን በማግለል፣ በሐሰት የኢትዮጵያ ብቸኛ ተወካዮች እንደኾኑ አድርገው ራሳቸውን አቅርበዋል፤” ሲሉ ከሰዋል። ቡድኖቹ አያይዘውም፥ “ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ እንደ ውጭ ዜጋ እንዲታዩ፣ የፈጠራ ትርክቶችን ካለማቋረጥ ያስተላለፋሉ፤” ሲል አክሏል ደብዳቤው።

ደብዳቤው በይቀጥላልም፣ የውጭ ጉዳይ ቢሮው፣ በመላ ኢትዮጵያ የሚያደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እና ድጋፍ፣ የሥራ ቅጥርንና አቅርቦቶችን፣ በሕዝብ ብዛት መሠረት ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በዕጥፍ እንዲጨምር ጠይቋል። በተጨማሪም፣ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ ፌዴራላዊ ሥርዐቱ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲኾን እንዲያበረታታ ደብዳቤው ጠይቋል።

ደብዳቤው በማከልም፣ የኦሮሞ ድርጅቶቹ፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙት የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ እና ሌሎችም የዲፕሎማሲ ሠራተኞች፣ መላውን የኢትዮጵያን ክፍሎች ያለአድልዎ ለማገልገል በሚያደርጉት ጥረት፣ ከጎናቸው እንደሚቆሙ አመልክቷል። በተጨማሪም፣ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ብዝኃነት ያላቸውን ብሔሮች እና ብሔረሰቦች እውቅና እንዲሰጥና አክራሪ ቡድኖች አገሪቱን እንደማይወክሉ እንዲያረጋግጥ እንጠይቃለን፤ ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት መሠረት፣ ኤምባሲው፥ “ፊንፊኔ” የሚለውን መጠሪያ መጠቀሙ አስፈላጊ እንደኾነ አጽንዖት የሰጠው የኦሮሞ ማኅብረሰብ ድርጅቶች ደብዳቤ፣ አምባሳደሩም፣ አምስቱንም ቋንቋዎች በመጠቀም ኢትዮጵያ ይበልጥ አካታች እንድትኾን ለሚያደርጉት ጥረት ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ አስታውቋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ፣ በአሜሪካ ድምፅ የዐማርኛ አገልግሎት ጥያቄ የቀረበለት ዐዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ በኢ-ሜይል በሰጠው መልስ፣ በአሁኑ ወቅት የሚሰጠው አስተያየት እንደሌለ ገልጿል።

ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በወጣው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ አንድ ላይ፣ “የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ርእሰ ከተማ ዐዲስ አበባ ነው፤” ይላል።

የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ፣ በ1987 ዓ.ም. ባወጣው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 6 ላይ፣ “የኦሮሚያ ክልል ርእሰ ከተማ ፊንፊኔ ነው፤” ሲል አስቀምጧል። ክልሉ በ2009 ዓ.ም. ባወጣው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ደግሞ፣ “የከተማው ስም ፊንፊኔ፣ ከዐዲስ አበበባ ጋራ እኩል መጠሪያ ይኾናል፤” ብሏል።

ቀደም ብለን የጠቀስነው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ በአንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ አንድ፣ “ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ፣ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋራ የሚቃረን ከኾነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፤” ሲል ደንግጓል።

አድማጮቻችንና ተመልካቾቻችን፣ በዚኽ ጉዳይ ላይ፣ የኹሉንም ወገኖች ሐሳቦች ያካተተና የሕገ መንግሥት ባለሞያዎችን አስተያየት የያዘ ቅንብር ይዘን ለመመለስ እየሠራን እንደምንገኝ እንገልጻለን።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

ዩክሬን አጋሮቿ የመካላከያ ምርቶቻቸውን እንዲያሳድጉ ጠየቀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:10 0:00

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG