በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የባይደን አሸናፊነት የተረጋገጠበት ሂደትና በምክር ቤቱ ህንጻ የተካሄደው አመጽ


የዩናይድ ስቴትስ ምክር ቤት ባለፈው ህዳር የተካሄደው የአሜሪካው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ዴሞክራቱ ጆ ባይደን መሆናቸውን ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

ምክር ቤቱ ማረጋገጫውን የሰጠው በትናንትናው እለት የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች፣ የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤትን በመውረር፣ ህገ አውጭዎቹ የምክር ቤት አባላት ስብሰባቸውን በማቋረጥ፣ ህንጻው ለቀው እንዲወጡ ካስገደዷቸው በኋላ፣ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ባደረጉት የድጋሚ ስብሰባ ነው፡፡

ተቋርጦ የነበረውን ስብሰባ የመሩት ምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ፣ የየክፍለ ግዛቶቹ ተወካዮች ለባይደን 306 እንዲሁም ለትራምፕ 232 ድምጽ የሰጡ መሆናቸው መረጋገጡን ይፋ አድርገዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ከትናንት ምሽት ጀምሮ እስከ ዛሬው ሀሙስ አጥቢያ ድረስ የክፍለ ግዛቶቹን ተወካዮችን ድምጽ ቁጥር ለማረጋገጥ ጥድፊያ ላይ ነበሩ፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች የምክር ቤቱን ህንጻ ከወረሩ ሰዓታት በኋላ ሁለቱም የዴሞክራቲክና የሪፐብሊካን ፓርቲ ህግ አውጭዎች የተመራጩን ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ቁርጠኞች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡

በትላንትናው እለት በሺዎች የሚቆጠሩ የትራምፕ ደጋፊዎች ከህግ አሰከባሪዎች ጋር ግብግብ በመፍጠር የተወካዮቹን ምክር ቤቶች ወረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚያው ምሽት፣ በጥድፊያ ወደ ምክር ቤቱ የተመለሱ ህግ አውጭዎች፣ ቀደም ሲል ያቋረጡትን ስብሰባ በመቀጠል የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድድር አሸነፊ የሆነውን ለመወሰን፣ በየክፍለ ግዛቱ ተወካዮች የተሰጠውን ድምጽ በመቁጠር አጽድቀዋል፡፡ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት መሪ ሚች መካኔል

“ለፕሬዘደንታዊው ምርጫ አሸናፊ ማረጋገጫውን እንሳጠለን” ብለዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ በህግ መወሰኛው ምክር ቤት ፕሬዘደንትነታቸው ባላቸው ሥልጣን በአመጹ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ስብሰባ ከሰዓታት በኋላ ሲያስጀምሩ

“ዛሬ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ታሪክ የጨለማው ቀን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ፖሊሶች፣ የፌደራል፣ የክፍለ ግዛቶችና የአካባቢው ህግ አስከባሪዎች ምስጋና ይግባቸውና እነሱ ባደረጉት ፈጣን ጥረት አመጹ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡” ብለዋል፡፡

ከመቶ በላይ የሚሆኑ የሪፐብሊካን ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና 14 የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት ከመነሻው ያሰቡት የተለየ ነገር ነበር፡፡ የምርጫውን ውጤት፣ በተለይም ባይደን አሸንፈዋቸዋል ባሏቸው 6 አሻሚ በተባሉ ክፍለ ግዛቶች ያለውን የማረጋገጫ ሂደቱን ማስተጓጎል ነበር፡፡ የምክር ቤቱ አባል ጃሽ ሀውሌይ በእለቱ ከታየው አመጽ ይልቅ

“ ስለምርጫችን ትክክለኝነትና ፍትሀዊነት፣ ባለፈው ህዳር ወር ስለሆነው ነገር ቅሬታ ላላችሁ ወገኖች ሁሉ ቅሬታን የማቅረቢያው ትክክለኛው መንገድ ይኽ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ትላንት ረቡዕ የተነሳው አመጽ፣ በርካታዎቹ ህግ አውጭ የምክር ቤት አባላት፣ ቀደም ሲል የነበራቸውን ተቃውሞ እንዲተው አድርጓቸዋል፡፡ተከታዩን የተናገሩት ሴነተር ኬሊ ከእነዚህ አንዷ ነበሩ፡፤

“ዛሬ በግልጽ የታየው ክስተት ውሳኔዬን እንደገና እንድመረምረው አድርጎኛል፡፡ የምርጫውን ውጤት የሚያረጋግጠውን ሂደት ለመቃወም አሁን ልቦናዬ አይፈቅድልኝም፡፡”

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይ ደን አመጹን ያወገዙ ሲሆን ከደለዌር ክፍለ ግዛት ዊሊምግተን ሆነው ባሰሙትን ንግግር፣ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ጠንካራ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

“ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ህገ መንግሥቱን ለመጠበቅ የገቡትን ቃለ መሃል በማክበር፣ አሁኑኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ወደሚሰራጭ ቴሌቪዥን ወጥተው ይህን የአመጽ ወረራ እንዲያስቆሙ ጥሪዬን አቀርባላችኋለሁ!”

ትራምፕ ትዊተር ላይ ባስተላለፉት በቪዲዮ የተቀዳ መልዕክታቸው መረጋጋት እንዲኖር ጥሪ ያስተላለፉ ቢሆንም፣ ምርጫው ተጭበርበሯል የሚለውን መሰረት የለሹን ክሳቸውን፣ እንደሚከተለው ማሳተላለፋቸውን ቀጥለውበታል፡፡

“ከዳር እስከዳር ያሸነፍንበት ምርጫ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ያውቀዋል፡፡ በተለይም በሌላ ወገን ያሉት፡፡ ለማንኛውም አሁን ወደ የቤታችሁ መሄድ አለባችሁ፡፡”

ትዊተርና ፌስ ቡክ የተባሉት ማህበራዊ የትስስር ድረገጾች፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሬዘዳንት ትራምፕ ድርጊት ፖሊሲያቸውን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ በድረ ገጾቹ የፕሬዚዳንቱን የግል መልዕክት ማስተላለፊያቸውን በመዝጋት አግደዋቸዋል፡፡ ትራምፕ ቀደም ሲል ደጋፊዎቻቸው ወደ ምክር ቤቶቹ እንዲያመሩ

“ከዚህ በኋላ ወደዚያው እንጓዛለን፡፡ እኔም እዚያው ከናንተ ጋር እገኛለሁ፡፡” በማለት አሳስበዋቸዋል፡፡

“ደካማዎቹን የምክር ቤት ሰዎች አስወግዱ” ብሎ ለደጋፊዎቻቸው መናገር ማለት ምን ማለት ነው ይላሉ፤ በቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም (A&M) ዩኒቨርስቲ ስለ ፕሬዚዳንታዊ ንግግሮች የሚያስተምሩት ጀኒፈር መርሲያ

“አመጹን አነሳስተዋል፡፡ በአካል ተገኝተው ባይመሯቸውም በንግግራቸው መርተዋቸዋል፡፡” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

17 ዴሞክራት የሆኑ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማይክ ፔንስ የህገ መንግስቱን ማሻሻያ አቀንጽ 25 በመጠቀም ትራምፕን በአስቸኳይ ከሥልጣናቸው እንዲያነሱ ጠይቀዋል፡፡ ትራም የፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ሊያበቃ ሁለት ሳምንታት የሚቀረው በመሆኑ የተፈጻሚ መሆኑ ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ በቺካጎ ዩኒቨርስቲ የህገ መንግሥት መምህር የሆኑት አዚዝ ኻክ እንዲህ ይላሉ

“እንደ እውነቱ ከሆነ የህገ መንግሥቱ ማሻሻያ አንቀጽ 25 የሚያነሳው ስለ ብቃት ማነስ እና በአካልም ሆነ በጤንነት ምክንያት ማልገል ስላለመቻል ነው እንጂ ስለፕሬዚዳንቱ የሥነልቡና ብቃት አይደለም፡፡”

ይሁ ሁሉ ሁከት ቢኖርም፣ ጆ ባይደን 46ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በመሆን፣ እኤአ ጥር 20/2021 በዓለ ሲመታቸውን ያከብራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባይደን

“እኔ ስለራሴ ደህንነት ወይም ፕሬዚዳንት የመሆኛዬ ቀን ስለሚከበርበት በዓለ ሲመቴ አይደለም የማስበው፡፡ እሱ አያሳስበኝም፡፡” ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል ህግ አውጭዎቹ የምክር ቤት አባላት የትናንቱን ሁከት በመቆጣጠር ከፍተኛ ተጋድሎ ይደረጉትን የፖሊስና ህግ አስከባሪ አካላት አድናቆታቸውን ቢገልጹም ቀድሞውኑም ቢሆን እንዲህ ያለ ነገር እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ በተለይም በአዲሱ ህግ አውጭ ምክር ቤት የምክር ቤቱን ህንጻና አስተዳደር በጀት ኮሚቴ የሚመሩት ሁለቱ ዴሞክራቶች

“ብዙ ቪዲዮች አሉ፣ አንዳንዶቹ ጀግንነትን የሚያሳዩ ቢሆንም አንዳንዶቹ ግን አሳሳቢ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡ “ሙሉ ምርመራ ተደርጎ የምክር ቤቱ ህንጻ በዚያ ፍጥነት እንዴት ሆኖ ሊወረር እንደቻለ የጥበቃውና የደህንነቱ ሁኔታ እንደገና ሊመረመር እንደሚገባውም” አሳስበዋል፡፡

“የፕሬዘዳንቱን መሰረት ቢስ ቅሰቀሳ ሰምተው ቀደም ሲል ለተቃውሞ አመጽ የተዘጋጁ ሰዎች መኖራቸው እየታወቀ ለምን በቂ ዝግጅት አልተደረገም” የሚሉም ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል የሆኑት ኢሃን ኦማር እንዲህ ብለዋል

"ለብሄራዊ ደህንነት ጥበቃ በቢሊዮን ዶላሮች እናወጣለን፡፡ በዛሬው እለት በአገሪቱ ምክር ቤት ላይ ህገ ወጥ ነውጠኞች ያደጉትን ወረራ ግን ማስቆም አልቻልንም፡፡ ይህ ተቀባይነት የለውም!"

ዘገባው በቪኦኤ ዘጋቢ ፓትሲ ውዳክስዋራ እና በቪኦኤ የዜና ክፍል ባልደረቦች ከተጠናቀሩት ዘገባዎች የተወሰዱ ናቸው፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

የባይደን አሸናፊነት የተረጋገጠበት ሂደትና በምክር ቤቱ ህንጻ የተካሄደው አመጽ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:26 0:00


XS
SM
MD
LG