በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመጨረሻ ጆ ባይደን ከምክር ቤት ማረጋገጫ አግኝተዋል


ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ እና የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ
ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ እና የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ

በትናንትናው ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ የተሰናባቹ ትረምፕ ደጋፊዎች ከሕግ አሰከባሪዎች ጋር ግብግብ ገጥመው የተወካዮቹን ምክር ቤት ቢወሩም ከሰዓታት በኋላ ተመልሰው ገብተው ስብሰባውን ያስቀጠሉት የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት ባለፈው ኅዳር የተካሄደው የአሜሪካው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ዴሞክራቱ ጆ ባይደን መሆናቸውን ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ደጋፊዎች፣ የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤትን በመውረር፣ ሕግ አውጭዎቹ የምክር ቤት አባላት ስብሰባቸውን በማቋረጥ፣ ህንጻው ለቀው እንዲወጡ ካስገደዷቸው በኋላ የምክር ቤቶቹ አባላት ሁኔታዎች ተመልሰው በቁጥጥር ሥር እስኪውሉ ጠብቀው ወደ ምክር ቤቱ በመግባት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ባደረጉት የድጋሚ ስብሰባ ማረጋገጫውን ሰጥተዋል።

በረብሻው ወቅት ከአዳራሹ እንዲወጡ ቢደረገም እዚያው ምክር ቤቱ ውስጥ መቆየታቸው የተነገረው ተሰናባቹ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ በአመፁ ምክኒያት ተቋርጦ የነበረውን ስብሰባ በድጋሚ ሲያስጀመሩ፤ “ዛሬ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ታሪክ የጨለማው ቀን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ፖሊሶች፣ የፌደራል፣ የክፍለ ግዛቶችና የአካባቢው ህግ አስከባሪዎች ምስጋና ይግባቸውና እነሱ ባደረጉት ፈጣን ጥረት አመጹ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።

በመጨረሻም የየክፍለ ግዛቶቹ ተወካዮች ለባይደን 306 እንዲሁም ለትራምፕ 232 ድምጽ የሰጡ መሆናቸው መረጋገጡን ይፋ አድርገዋል፡፡

XS
SM
MD
LG