በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአሜሪካ ምርጫ ኒኪ ሄሊ ከውድድሩ ወጡ


የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር ኒኪ ሄሊ እአአ መጋቢት 6/2024
የሪፐብሊካን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደር ኒኪ ሄሊ እአአ መጋቢት 6/2024

ትናንት ማክሰኞ በተካሄደው “ሱፐር ቱስዴይ” የቅድመ ምርጫ ውጤት፣ የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ እና በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በየፓርቲያቸው ያላቸውን መሪነት ሲያጠናክሩ፣ የትረምፕ ተፎካካሪ የሆኑትና እጅግ አነስተኛ ድምፅ ያገኙት ኒኪ ሄሊ ከውድድሩ መውጣታቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት፣ ቀድመው አገረ ገዢ በነበሩባት የደቡብ ካሮላይና ግዛት በምትገኘው ቻርልስተን ከተማ፣ ከምርጫው መውጣታቸውን አስመልክተው ንግግር ያደረጉት ኒኪ ሄሊ፣ ተፎካካሪያቸውየነበሩትን ትረምፕ እንደሚደግፉ አላስታወቁም።

ባይደን ትናንት ምርጫ ከተደረገባቸው 15 ክፍለ ግዛቶች ውስጥ፣ በሰላማዊ ውቅያኖስ ከምትገኘው የአሜሪካ ግዛት ሳሞዋ ደሴት በስተቀር በሌሎቹ አሸንፈዋል።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ትረምፕ በ 14 ግዛቶች እንዳሸነፉ ሲታወቅ፣ የሪፐብሊካኑን ፓርቲ ለመወከል ሲፎካከሯቸው የሰነበቱት ኒኪ ሄሊ የቬርሞንት ክፍለ ግዛትን ብቻ አሸንፈዋል። ሄሊ ሁለት ግዛቶችን ብቻ ነበር ያሸነፉት፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት በቅድመ ምርጫው ሳይቀናቸው ቢቀርም፣ “ትረምፕ መልሰው ሥልጣን ላይ የሚመጡ ከሆነ፣ ለአገራችን አይበጅም” በሚል ውድድራቸውን ቀጥለው ነበር።

በሥልጣን ላይ እንዳለ ፕሬዝደንት ከፓርቲያቸው ብዙም ተፎካካሪ የሌለባቸው ባይደን፣ በህዳር ወር ለሚደረገው ምርጫ ትረምፕን በድጋሚ ለመግጠም በዝግጅት ላይ ናቸው።

“ትረምፕ መልሰው ወደ ሥልጣን ከመጡ፣ ብጥብጥ፣ መከፋፈል፣ ጨለማ ይሰፍናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል ባይደን።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG