ወደ አራት ወራት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ በኮቪድ-19 የሞቱትን ከመቶ ሺህ የላቀ ቁጥር ያላቸውን አሜሪካዊያን በክብር ለመዘከር የፊታችን ሰኞ ብሔራዊ የኀዘን ትውስታ ጊዜ እንዲታወጅ የሁለቱም ገዥ ፓርቲዎች እንደራሴዎች የሚገኙበት አንድ የሴናተሮች ስብስብ ጉትጎታውን አጠናክሯል።
“ሃገራችን ይህንን የጭለማ ጊዜ በአንድነትና በጠራ አዕምሮ ማሰብ አለባት - ብለዋል ዴሞክራቲኩ ሴናተር ብራያን ሻልትዝ - በዚህ ሊታሰብ የማይችል የጉዳት ጊዜ እያንዳንዷን ሕይወት ቆም ብለን ማክበር፤ አብረንም ማዘን ይገባናል”
ሪፐብሊካኗ ሴናተር ሊሳ መርኮውስኪ ደግሞ “የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሃገራችን ላይ እጅግ የከበደ መከራ አድርሷል፤ እጅግ ብዙ ቤተሰቦች የሚወድዷቸው ሲሰቃዩ አይተዋል። በወረርሽኙ ምክንያት የተከተለው መዘጋትም በፈጠረው የበረታ መለያየት ዘመድ ወዳጆቻቸውን ያጡ ሁሉ ለቤተሰቦቻቸው ኀዘን ለመቀመጥ አልቻሉም፤ የመጨረሻውን ስንብት ወግ ለማድረስና እርማቸውን ለማውጣት እንኳ አልታደሉም” ብለዋል።
በሕግ መምሪያው ውስጥ የቀረበ ሌላ ሃሣብ ደግሞ እንደራሴዎቹ ሸንጎ በተቀመጡ ቁጥር በየዕለቱ የኅሊና ፀሎት እንዲያደርጉ፤ ወረርሽኙ ካበቃ በኋላም ስላለፉት ብሄራዊ የኀዘን ቀን እንዲታወጅ ይጠይቃል።
ከዓለም የኮሮናቫይረስ መዛመት መጠንና ከኮቪድ-19 ሞትም ወደ ሲሦ የሚሆነው የደረሰው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነው።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።