በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የኢትዮጵያ መንግሥት መንገዱን በፍጥነት መቀየር አለበት” የአሜሪካዊው ኮንግረስማንና የኢትዮጵያ መንግሥት ትግል


የኑ-ጀርሲ ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት
የኑ-ጀርሲ ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት

የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹን መብት እንዲያከብር መልካም አስተዳድርና ዴሞክራሲን እንዲገነባ የሚጠይቅና የዩናይትድ ስቴይትስ መንግስት ኢትዮጵያን ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር እንዲገነባ የሚደነግግ ረቂቅ ውሳኔ በኮንግርስ እንደገና ቀረበ።

የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታ በፅኑ የሚኮንነው ረቂቅ ውሳኔ በሕግ አውጭው የኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስ ስሚት ፀኃሃፊነትና በሌሎች አጋርነት ነው በድጋሚ ለውሳኔ የቀረበው።

በዩናይትድ ስቴይትስ አዲስ አስተዳድር ከተመሰረት አንድ ወር አልፎታል። የህግ አርቃቂና የህግ አጽዳቂው ኮንግረስም ሆነ የህግ አስፈጻሚው መንግስቱ በሪፐብሊካን ፓርቲው ቁጥጥር ስር ነው።

ሪፐብሊካኑ የኑ-ጀርሲ ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት የሕግ አርቃቂውን የውጭ ጉዳዮች የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ ይመራሉ። በኢትዮጵያ ላይ የጻፉት ረቂቅ ህግ በሌሎች የኮንግረስ አባላት ዴሞክራቶችን ጨምሮ ድጋፍ ያለው እንደሆነ ተገልጿል።

ክሪስ ስሚት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞትና የአስተዳድር እክሎችን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ፖሊሲ ሲቀርጹ የቆዩ ፖለቲከኛ ናቸው።

“አዲስ ረቂቅ ውሳኔ ይዘናል። ማይክ ኮፍማንና ሌሎች የኮንግረስ አባል የሕዝብ ተወካዮችም ድጋፋቸውን ሰጥተውታል። ሕጉን አስተዋውቀናል፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሁኔታን ለማሻሻል ወሳኝ ሕግ ይሆናል የሚል እምነት አለን። መንግሥቱ በአሁኑ ወቅት እጅግ የከፋ አዘቅት ውስጥ ይገኛል። ሰዎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ የሰቆቃ ግርፋቶች አሉ፤ ስለዚህ ይሄ ሁሉ በቃ እያልን ነው” ብለዋል።

በመስከረም ወር የኒውጀርሲው ሪፐብሊካን ኮንግረስማን ከሌሎች ዴሞክራቶች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ረቂቅ ህግ አስተዋውቀው ነበር። በዚያን ወቅትም “በቃ” የሚል መልዕክት ነበር ያስተላለፉት በአዲስ መልኩ የቀረበው ሕግ፤ እንደገና ለውሳኔ ሲቀርብ፤ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ትገኛለች። ውሳኔም ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታስ ክሪስ ስሚት እንዴት ያዩታል?

“ሁኔታዎች ክፉኛ አሽቆልቁለዋል። አወን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደ ማስመሰያ ምክንያት ነው የማየው። በእርግጥ በሀገሪቱ ችግሮች አሉ፤ በሌሎች ሀገሮችም እንዲሁ ፈተናዎች አሉ። በኢትዮጵያ ግን የፀጥታ ስጋትን እንደከለላ በመጠቀም በአዋጅ ዜጎችን ማሸማቀቅና በማስፈራራት የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘውን መንገድ አሁኑኑ በፍጥነት መቀየር አለበት።”

በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲን ምላሽ ጠይቀናል።

በኮንግረሱ ረቂቅ ውሳኔ ለኮንግረስ ጠረጴዛ ሲቀርብ፤ ዝርዝሩን ተመልክተን አስተያየት እንሰጣለን ሲሉ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ቃል አቀባይ አቶ ተስፋየ ወልዴ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታና አስተዳድራዊ ሁኔታን በማጤን ዩናይትድ ስቴይትስ ልትከተል የሚገባትን የፖሊሲ አቅጣጫ በሕግና ውሳኔ ለማፅናት ያሰቡ ረቂቆች በኮንግረስ አባላት ሲወጡ፤ ኢምባሲው በረብጣ ዶላር የኮንግረስ ድጅ ጠኝ ወትዋቾችን ቀጥሮ ሲከላከል ቆይቷል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ የሚኖራቸው ፖሊሲ ምን እንደሚሆን ብዙዎችን እያነጋገር ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት፤ የሰብዓዊ እርዳታን አስመልክቶ ለውጥ እንደማይኖር ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ሲናገሩ፤ መልካም አስተዳድርና ዴሞክራሲን አስመልክቶ ከኮንግረስ ለትራምፕ አስተዳድር የሚተላለፉ መልእክቶችን እንዲህ አብራርተዋል።

“ተስፋችን በዚህ ሂደት ውስጥ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ እንጽፋለን፤ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከታወቁ በኋላ፤ በኢትዮጵየ የምንከተለውን ፖሊሲ ከላይ እስከታች እንደገና መገምገም አለበን የሚል መልእክት እናስተላልፋለን” ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት ብለዋል።

ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት በኢትዮጵያ ጉዳዮች በርካታ ሕጎችን ያስረቀቁና፣ በተደጋጋሚ የምስክር ሰሚ ሸንጎዎችን ያስቻሉ ሕግ አውጭ ናቸው።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ሪፐብሊካኑ ኮንግረስማን ክሪስ ስሚት
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:59 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG