የፌደራል የምርመራ ቢሮ/ኤፍ.ቢ.አይ ድሬክተር ክሪስቶፈር ሬይ፣ እኤአ ጥር 6 በምክር ቤቱ ህንጻ የተካሄደው ሁከትና ብጥብጥ፣ የጆ ባይደንን የምርጫ ውጤት ለመቀልበስ በትራምፕ ደጋፊ አመጸኞች የተደረገ የአገር ውስጥ ሽብርተኝነት ሲሉ በትናንትናው ዕለት ለዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ድምጽ የምክር ቤቱ ዘጋቢ ካትሪን ጊብሰን እንደዘገበችው ድሬክተሩ ቢሮው ስለ አመጹ የሚያስረዳ ዝርዝር መረጃ አስቀድሞ የደረሰው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እኤአ ጥር 6 በዩናይትድ ስቴትስ፣ ምክር ቤት ህንጻ ላይ ከተካሄደው የአመጽ ጥቃት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ ባለሥልጣናት ጥቃቱ የአገር ውስጥ ሽብርተኝነት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መነሻውም የነጭ የበላይነትን በሚያራምዱ ወገኖች የተካሄደ መሆኑን አስታወቀው በአሜሪካ ደህንነት ላይ ስጋት የደቀነ መሆኑንም እንደሚከተለው ገጸዋል፡፡
“ዘርን መሠረት ካደረጉ አመጾችና አክራሪነት ይኸኛው ትልቁ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ሽብርተኝነትን አስመልክቶ ከመረመርናቸው ጉዳዮችም በብዛቱ ይኸኛው ይበልጣል፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ህይወት ከሚጠፋባቸው ጥቃቶች ውስጥም አብዛኛው የተፈጸመው በእነዚሁ ተመሳሳይ ቡድኖች ነው፡፡”
ሬይ የአመጽ ጥቃቱ ከተካሄደ ወዲህ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ማብራሪያ፣ በአመጹ የተሳተፉ ሰዎች የመጡት ከተለያዩ ቡድኖች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህም የነጭ የበላይነትን የሚያከሩና ነውጠኛ ሚሊሻዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የትራምፕ ተቃዋሚ ሆነው ሳለ ራሳቸውን ደብቀው የተቀላቀሉ ግራ አክራሪ ቡድኖች አሉበት ለተለባለው ግን ምንም ዓይነት መረጃ የሌለ መሆኑን እንደሚከተለው አስረድተዋል
“ሁሉንም አክራሪ አመጸኞችና ርእዮተ ዓለሞቻቸውን በእኩል ዓይን የምንመለከት ቢሆንም እስካዛሬ ካየናቸው የአክራሪ አመጸኞች መካከል እኤአ ጥር 6 ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ አንቲፋ በሚል የተመዘገቡ አመጸኞች ምንም ዓይነት ግ ንኙነት ያላቸው ሆኖ አላገኘንም፡፡ ይህ ማለት ግን ለወደፊቱ አንመለከትም ማለታችን አይደለም፡፡ ማየታችንን እንቀጥላለን በአሁኑ ወቅት ግን ምንም ያየነው ነገር የለም፡፡”
የኤፍ ቢ አይ ድሬክተሩ ሬይ፣ እስከዛሬው እለት ከአመጹ ጋር ተያይዞ ከ270 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ክስ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው ምርመራው እየቀጠለ እንደሚሄድም ሲናገሩ ይህን ብለዋል፦
“ብዙ ጉዳዮች እየተገለጡ ስለሆነ አዳዲስ ክሶችም በየቀኑ እየተመሰረቱ ነው ማለት ይቻላል፣ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች የፈለገውን ያህል ቢሆኑም ኤፍ ቢ አይ ግን እነዚህ ነገሮች በጥልቀት ሊያያቸው ቆርጦ ተነስቷል፡፡”
ይሁን እንጂ ብዙ የሪፐብሊካን አባላት፣ የግራ አክራሪዎቹ የሚያካሂዱት የአገር ውስጥ ሽብርተኝነት፣ ከዚህኛው እኩል ምናልባትም የበለጠ መሆኑን እንደ አንቲፋ የመሳሰሉትን አክራሪ ወገኖች በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
ለክርክራቸውም ባላፈው የበጋ ወቅት፣ በኦረገን ክፍለ ግዛት ፖርትላንድ ውስጥ በተካሄደው አመጽ የተቃጠለውን የፌደራል ፍርድ ቤት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ የሪፐብሊካን የምክር ቤት አባል ሴነተር ቴድ ክሩዝ እንዲህ ይላሉ
“ባላፈው ዓመት ውስጥ እጅግ በርካታ የሆኑ የአክራሪዎችን ሁከትና ብጥብጦችን አይተናል፡፡ ብዙዎቹ የመላ አገሪቱን ጎዳናዎች የተቆጣጠሩት ግራ አክራሪዎች ናቸው፡፡”
ዴሞክራቶቹ ይህን ንጽጽር አይቀበሉትም፡፡ የዘር መድልዎን ለመቃወም በተካሄደ አመጽ የተፈጸመ ህገ ወጥነትን የነጭ የበላይነትን ከሚያራምዱ አመጸኞች ጋር ማነጻጸሩ ልክ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡
የህግ መወሰኛው ምክር ቤት የፍትህ ኮሚቴ ሊቀመንበር ዴሞክራቱ ዲክ ደርባን እንዲህ ይላሉ
“ይህ የምርጫን ውጤት ለመገልግበጥ ከተነሳ አመጽ ጋር እኩል አይደለም፡፡ ወይንም የንኡሳን የህብረተሰብ ክፍልን ዒላማ በማድረግ በጅምላ ለመፍጀት ተኩስ መክፈት አይደለም፡፡ ይህ በሀሰት የሚደረግ ንጽጽር፣ እኤአ ጥር 6 ህይወታቸውን ያጡትንም ሆነ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ጀግኖቹን የፖሊስ መኮንኖች መስደብ ነው፡፡”
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምስክርነት፣ የምክር ቤቱ ህንጻ ጥበቃ ባለሥልጣናት፣ እኤአ ጥር 5 የአመጽ ጥቃቱ ሊፈጸም እንደሚችል ከኤፍ ቢ አይ የተላከውን ማስጠንቀቂያ ያልደረሳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የኤፍ ቢ አይ ድሬክተር የተባለው ማስጠንቀቂያ ተነቦ ቢሆን ኖሮ የጸጥታው ሁኔታ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል መላ መምታት አልፈለጉም፡፡
የደረሰውን የአመጽ ጥቃት ለመመርመር ይቋቋማል የተባለውን ኮሚሽን አስመልክቶ፣ እየተካሄደ ያለው ድርድርና የጸጥታ ጥበቃን ለማጠናከር የቀረቡት ሀሳቦች ቢኖሩም፣ በሚቋቋመው ኮሚሽን ውስጥ የዴሞክራቶች ቁጥር በርክት እንዲል በሚፈልጉት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ናንሲ ፕሎሲ ለጊዜው እንዲገታ ተደርጓል፡፡