በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካና የእንግሊዝ ጦር በየመን የሁቲ ወታደራዊ ኢላማዎችን ደበደቡ


ፎቶ ፋይል፦ የሁቲ ተዋጊዎች አሜሪካ በየመን ላይ የምታደርገውን ጥቃት በመቃወም ሰልፍ አድርገው ሰንዓ፣ የመን እአአ ጥር 23/2024
ፎቶ ፋይል፦ የሁቲ ተዋጊዎች አሜሪካ በየመን ላይ የምታደርገውን ጥቃት በመቃወም ሰልፍ አድርገው ሰንዓ፣ የመን እአአ ጥር 23/2024

የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያ ጦር ሠራዊት የመን ውስጥ በኢራን የሚደገፉ ሁቲዎች በሚጠቀሙባቸው ስምንት ቦታዎች ላይ ያሉ በርካታ ኢላማዎችን ትናንት ሰኞ ማምሻው ላይ ደብድበዋል።

ሁለቱ አጋሮች በአማጽያኑ የሚሳኤል ጥቃት የማድረስ አቅም ላይ የተቀናጀ የአጸፋ ምላሽ ሲወስዱ ያሁኑ ሁለተኛቸው ነው።

እንደ ባለሥልጣናቱም ገለጻ፣ የሁቲዎችን የሚሳይል ማከማቻ ሥፍራዎች፣ የሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና የሚሳይል ማስወንጨፊያዎችን ለማውደም የጦር መርከቦችን፣ ከባህር ሰርጓጅ መርከቦች የሚወነጨፉ ቶም ሃውክ ሚሳኤሎችን እና ተዋጊ ጄቶችን ተጠቅመዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊ ዘመቻውን አስመልክቶ በሰጡት ተጨማሪ አስተያየት፣ የደህንነት መረጃዎችን እና ክትትሎችን ጨምሮ አውስትራሊያ፣ ባህሬን፣ ካናዳ እና ኔዘርላንድስ ለተልዕኮው የየበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ስድስቱ አጋር ሃገራት በጋራ ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጥቃቱ በተለይ የሁቲዎችን ከምድር በታች ያለ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ሥፍራዎች እና እንዲሁም የሚሳይልና የአየር ክትትል ከማድረግ አቅማቸው ጋራ የተገናኙ ቦታዎች ላይ የተነጣጠረ እንደነበር ተናግረዋል።

ዓላማቸው ውጥረቱን ማርገብና በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን ሁኔታ ወደ ቀደመ ይዞታው መመለስ እንደኾነ አክለዋል።

“ይሁንና በዓለም ላይ በእጅጉ አስፈላጊ በሆነው የባሕር መስመር ነፃ የንግድ ልውውጥን የሚያደናቅፉ እና በሕይወት ላይ አደጋ የሚደቅኑ ቀጣይ አዝማሚያዎችን ለመከላከል የማናመነታ መሆኑን በመግለጽ የሁቲ አመራሮች በድጋሚ ማስጠንቀቅ እንሻለን” ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG