በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶርያን የሰላም ስምምነት ለሚከታተለው ቡድን ዕውቅና ሰጠ


የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶርያን የሰላም ስምምነት ለሚከታተለው ቡድን ዕውቅና ሰጠ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:01 0:00

የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶርያን የሰላም ስምምነት ለሚከታተለው ቡድን ዕውቅና ሰጠ

የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እንዲከታተል ያቋቋመው ተቆጣጣሪ ቡድን፣ በእስከ አሁኑ የትግበራ ሒደት ለፈጸማቸው ተግባራት፣ ዛሬ ዕውቅና ሰጥቶታል።

የዩናይትድ ስቴት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመርም፣ ቡድኑ በሰላም ስምምነቱ ትግበራ ላይ “ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፤” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተካሔደው የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግምገማ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ለስምምነቱ የተሟላ ትግበራ ቁርጠኛ መኾናቸውን ገልጸዋል፤ በጥቂት ወራት ውስጥም ዳግም ለመገናኘት መወሰናቸው ታውቋል።

የአውሮፓ ኅብረት እና የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ኤምባሲዎችም፣ ዛሬ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ሁለቱም ወገኖች ለስምምነቱ ቀጣይ አተገባበር አሳይተዋል ያሉትን ቀና አቋም በአዎንታ እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ኅብረት፣ በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሪቶርያ የተፈረመውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እንዲከታተል ያቋቋመው ተቆጣጣሪ ቡድን፣ በእስከ አሁን የትግበራ ምዕራፍ የነበረውን ሚና አድንቆ ለቀሪ የክትትል ተግባራቱም ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡

ኅብረቱ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ በታኅሣሥ ወር 2015 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ የተቋቋመውና 21 ወታደራዊ እና ሲቪል ባለሞያዎችን በአባልነት የያዘው ተቆጣጣሪ ኮሚቴ፣ በቀጣይ የሥራ ጊዜው በስምምነቱ መሠረት፡- ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት እና የሲቪል ሰዎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ ክትትል ያደርጋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማሃመት፣ የተቆጣጣሪ ኮሚቴው አባላት አፍሪካዊ አንድነትን በሚያሳይ መልኩ ፈጽመዋቸዋል ላሏቸው ሥራዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም፣ የአፍሪካ ኅብረት ስምምነቱ በተሟላ ይዘቱ እንዲተገበርና በኢትዮጵያውያን የሚመራና ዘላቂ ሰላምን የሚያሰፍን ሒደት እንዲጠናከር እንደሚያበረታታም አመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪው የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ፣ የሜዳልያ ሽልማት ያገኙ የስምምነቱ ትግበራ ተቆጣጣሪዎችን፣ “የተሰጣችኹ ሽልማት ለአፍሪካ እና ለሕዝቧ እስከ አሁን ላበረክታችኹት አስተዋፅኦ እና በቀጣይ ለምትፈጽሙት ነው፤” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ለመበተንና ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል የሚያግዛት አንድ ሚሊዮን ዶላር የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ፈንድ ድጋፍ ማግኘቷን የጠቀሱት የጠቀሱት ደግሞ፣ የኅብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮችና የሰላምና የፀጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዱኤ ናቸው። የሰላም ፈንዱ የመጀመሪያዋ ተቀባይ ሀገር እንደኾነችም ተናግረዋል፡፡

ከትላንት በስቲያ ሰኞ በተጀመረው የሰላም ስምምነቱ የአፈጻጸም ግምገማ ላይ የተገኙት የዩናይትድ ስቴት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ በኬኒያዊው ጀነራል ራዲና የሚመራው የኅብረቱ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ፣ በስምምነቱ ትግበራ ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ገልጸው አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ዘላቂ ሰላም በማምጣት ዙሪያ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ በተለይ፣ ታጣቂዎችን የመበተንና ወደ ኅብረተሰቡ የመቀላቀል፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ፣ በሽግግር ፍትሕ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአጽንዖት አንሥተዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ተወካዮች ስምምነቱ በምልኣት ለመተግበር ዝግጁነታቸውን ማረጋገጣቸውን አስታውቋል፡፡ በትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታን ለማጠናከር እንደሚሠሩ ሁለቱም አካላት መናገራቸውን ጠቅሶ፣ በቅርብ ወራት የስምምነቱን አፈጻጸም የሚገመግም ተመሳሳይ ውይይት እንደሚካሔድም ኅብረቱ አስታውቋል::

በአዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ የቡድን 7 አገራት እና የአውሮፓ ኅብረት ልኡካን በጋራ ባወጡት መግለጫ በበኩላቸው፣ የሰላም ስምምነቱ ትግብራ ለመገምገም ከትናንት በስትያ ሰኞ የተካሄደውን ውይይት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

መግለጫው አክሎም፣ “የሰላም ስምምነቱ በመፈረሙ የጥይት ድምፅ ቆሟል፣ ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፣ በክልሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም ተጀምሯል” ብሏል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት በበጎ እንደሚታይ መግለጫው ጠቁሟል።

ከዚህ በኋላም ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን ለመበተን እና መልሶ ወደ ሕብረተሰቡ ለመቀላቀል በጀት መመደብ፣ በጦርነቱ ለተጎዱ አቸኳይ ድጋፍ ማቅረብ፣ የመልሶ ግንባታ ሥራ መሥራት፣ ተጎጂዎች ማእከል ያደረግ የሽግግር ፍትሕ መኖር እና ተጠያቂነት መኖር እንደሚገባው በመግለጫው ተነስቷል።

በተጨማሪም ደህንነቱ የተጠበቀ እና በፍቃደኝነት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ ይገባል ብለዋል::

የቡድን ሰባት አባል አገራት እና የአውሮፓ ህብረት በመግለጫቸው የአፍሪካ ህብረት ያቋቋመው ስምምነቱ የሚከታተል ተቆጣጣሪ ቡድን እስካሁ አከናውኗል ያሉትን ተግባራት አድንቀዋል። በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች ያሉት ግጭቶችም በተመሳሳይ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል::

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG