በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተባበሩት መንግሥታት የንዩክሌር መርማሪዎች በዛፖሮዥዢያ ሥራቸውን ጀምረዋል


የተባበሩት መንግሥታት የንዩክሌር ባለሙያዎች ቡድን የጥንቃቄና የደኅንነት አባላት በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን ኤነርሆዳር የሚገኘውን የዛፖሪዝሂሂያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫን ሲጎበኙ።
የተባበሩት መንግሥታት የንዩክሌር ባለሙያዎች ቡድን የጥንቃቄና የደኅንነት አባላት በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን ኤነርሆዳር የሚገኘውን የዛፖሪዝሂሂያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫን ሲጎበኙ።

በዛፖሮዥዢያ የንዩክሌር ኃይል ማመንጫ አካባቢ በሩሲያና በዩክሬን ኃይሎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት የንዩክሌር ባለሙያዎች ቡድን ትናንት ሐሙስ የመጀመሪያውን የጥንቃቄና የደኅንነት ጉብኝቱን ማካሄዱን የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ባለው የንዩክሌር ኃይል ማመንጫ አቅራቢያ በሚገኘው ኤነርሆዳር ወረዳ ውስጥ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መካሄዱም በመግለጫው ተገልጿል።

ተቆጣጣሪ ባለሙያዎቹ ዛሬም ሥራቸውን ይቀጥላሉ ብሏል መግለጫው።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በየምሽቱ በሚያተላልፉት ዕለታዊ መልዕክታቸው “ይህ ተልዕኮ እንዲሳካ ዩክሬን ሁሉንም ነገር አድርጋለች። ወራሪዎቹ ግን መርማሪዎቹ ተቋሙን ለመመልከት የሚያደርጉትን በጣም አስፈላጊ ተልዕኮ ፍሬ ቢስ ጉብኘት ለማስመሰል የሚያደርጉት ሙከራ መጥፎ ነው። ይህ እንደማይሳካ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

14 አባላት ያሉትን ተቆጣጣሪ ቡድን የሚመሩት የዓለምአቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ትናንት ሐሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “በአውሮፓ ትልቁ በሆነው የንዩከሌር ተቋም ሥራችንን ያለማቋረጥ እንቀጥላለን” ብለዋል።

ግሮሲ አክለውም “የተቋሙ አካላዊ ደኅንነት በተደጋጋሚ ተጥሷል” ማለታቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል ሩሲያ ከሌሎች አገሮች ጋር በመሆን ትናንት የጀመረችው ቫስቶክ 22 የሚባለው የስትራቴጂክ ጦር ልምምድ “ትላልቅና የተወሳሰቡ ወታደራዊ ልምምዶችን ማከናወን አልቻለም” ሲል የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል።

“እንደዚህ ያሉ ዝግጅቶች አስቀድመው ተፅፈው የተዘጋጁ፣ ተነሳሽነትን የማይጋብዙ፣ በዋናነት የሩሲያን መሪዎችና ዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ ለማስደሰት የታለሙ ናቸው” ብሏል መግለጫው።

XS
SM
MD
LG