በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምስራቅ አፍሪካ ከተሞች የሚኖሩ ስደተኞች ከኮቪድ-19 ጫና ጋር ግብግብ ይዘዋል


በዩጋንዳ ካምፓላ ውስጥ በስደተኝነት የሚገኙና ኮቪድ ተፅኖ ያሳደረባቸው ሁለት እናቶች| © UNHCR/Duniya Aslam Khan|
በዩጋንዳ ካምፓላ ውስጥ በስደተኝነት የሚገኙና ኮቪድ ተፅኖ ያሳደረባቸው ሁለት እናቶች| © UNHCR/Duniya Aslam Khan|

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክኒያት በገቢያቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳደረባቸው በአፍሪካ ቀንድና በታላላቅ ሐይቆች አካባቢ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ስደተኞች ተስፋ ወደ መቁረጥ እያመሩ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር) ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በመንግሥታት በተላለፉት የእንቅስቃሴ ገደቦች መመሪያ እና የሰዓት እላፊ ውሳኔዎች ምክኒያት በከተማ የሚኖሩ ስደተኞች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ባለመቻላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂ መኾናቸን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር) አስታወቀ።

የድርጅቱ ቃል- አቀባይ ቻርሊ ያክስሊ ለአሜሪካ ድምፅ ስለ ሁኔታው ሲናገሩ እነዚህ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ለከፍተኛ ዕዳ፣መዳረጋቸውን ተናግረዋል። “እንደ ወሲብ ንግድ ወይም የሕፃናትን ጉልበት ለብዝበዛ ወደሚዳርጉ ተስፋ አስቆራጭ ውሳኔዎችም ሊያመሩ ይችላሉ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አያይዘውም “የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች የንግድ ተቃማት እንዲዘጉ ወይም የሥራቸውን ስፋትና ጊዜ እንዲቀንሱ በመደረጉ ምክኒያት ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል። አብዛኞቹ ስደተኞች በቀን ሥራና መደበኛ ባልሆነ የንግድ ሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የነበሩ በመሆናቸው ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትም ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ ነበር።” ያሉት ቃል አቀባዩ ያክስሊ “አብዛኞቹ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ደግሞ በጣም በተጨናነቀና ፅዳታቸው ባልተጠበቀ አካባቢ ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው ለቫይረሱ ስርጭ በጣም ተጋጭ ናቸው።” ብለዋል።

ቃል- አቀባዩ ቻርሊ ያክስሊ አያይዘው በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ የሚኖሩት በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በቆሸሹና በቂ የሆነ ንፁህ የውሃ አቅርቦት በሌለበት አካባቢዎች የሚኖሩ በመሆናቸው በየጊዜው እጃቸውን መታጠብ አይችሉም ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድና በታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የሚገኙ መንግሥታት ለኮቪድ -19 ምላሽ ያወጡት እቅድ ስደተኞችን ያካተተ መሆኑን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ። “በዚህም ምክኒያት እነዚህ ስደተኞች ከዜጎች እኩል ምርመራ እና ሕክምና ማግኘት ይችላሉ።” ብለዋል ።

“ስለዚህ ዛሬ ለመንግሥታት የምናቀርበው ጥሪ እነዚህ የከተማ ላይ ስደተኞች በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ዜጎችን ታሳቢ ባደረጉ የሴፍቲ ኔት ፕሮግራሞች እንዲታቀፉ ነው።” ያሉት ቻርሊ ያክስሊ “ይህም ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ ነገር የሚያሟሉበት የእርዳታ ገንዘብ እንዲያገኙ፣ የቤት ኪራይ እንዲከፍሉ፣ መጠለያ እንዲኖራቸውና ምግብም መግዛት እንዲችሉ ያደረጋቸዋል።” ብለዋል።

የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር) እንደሚለው በወረርሽኙ ምክኒያ ምግብ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አዳጋች በመሆኑ የምግብ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ የተዛመተው የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ባለው የሰብል ውድመት ምክኒያት፤ ረሃብ ሊከሰት ድህነትም ሊስፋፋ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ።

ይህ በቀጠናው ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ የሚገኘውን ችግር የባሰ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የሕይወት አድን እርዳታዎችን ለማድረግ 126 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያፈልገው ገልጿል። ለዚህ እርዳታም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ክፍል እንዲረባረብና የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቋል።

|ሊሳሽ ላይን ከጄኔቫ ያጠናቀረችችውን ዘገባ ጽዮን ግርማ ወደ አማርኛ መልሳዋለች።|

XS
SM
MD
LG