በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስደተኞችንና ነዋሪዎችን ያስተሳሰረው የጋምቤላ የውኃ ፕሮጀክት


ስደተኞችንና ነዋሪዎችን ያስተሳሰረው የጋምቤላ የውኃ ፕሮጀክት
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:13 0:00

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት(ዩኤንኤችሲአር)፣ በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል፣ ኢታንግ ከተማ ያስገነባው ዐዲስ የውኃ ፕሮጀክት፣ በአካባቢው ተጠልለው የሚኖሩ ስደተኞችን ጨምሮ ከ260 ሺሕ በላይ የሚኾኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ በስደተኞች እና በአስጠጓቸው ማኅበረሰቦች መሀከል በፕሮጀክቱ ለመፍጠር የታለመው ትስስርም በመጠናከር ላይ እንደኾነ ተገልጿል።

ዐዲሱ የውኃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ንጹሕ ውኃ ለማግኘት ይቸገሩ ነበር። አሪየት፣ በውኃ ችግር ይሠቃዩ ከነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዷ ናት።

“በፊት ውኃ የምንቀዳው ከወንዝ ስለነበርና ንጹሕ ስላልኾነ በጣም እንቸገር ነበር፤” የምትለው አሪየት፣ “በተለይ ደግሞ ደረቅ በሚኾንበት ወቅት፣ ውኃው በጣም ይቆሽሻል፤ ለመጠጣትም በጣም ያስቸግራል። ሌላ ለንጹሕ ውኃ የሚያገለግል ምንጭ ስላልነበር እንጠጣዋለን። አሁን ግን ይህን ንጹሕ ውኃ በማግኘታችን በጣም ተደስተናል። በጣም እያገዘን ነው፤” በማለት በውኃ ፕሮጀክቱ መደሰቷን ገልጻለች።

ፕሮጀክቱ፣ በአካባቢው የተጠለሉ ስደተኞችም፣ የኅብረተሰቡ አካል መኾናቸው እንዲሰማቸው ከማድረጉም በላይ፣ ለሕይወት አስፈላጊ የኾነውን ውኃ በቀላሉ ለማግኘት እንዳገዛቸው ተናግረዋል። ራቼል፣ ከደቡብ ሱዳን ተፈናቅላ የመጣች ስደተኛ ናት፡፡ “ከማኅበረሰቡ ጋራ ውኃን ከአንድ መስመር ስንጋራ፣ ምንም ዐይነት መድልዎ አይኖርም። እነዚኽ ስደተኞች፣ እነዚያ ደግሞ የማኅበረሰቡ ነዋሪ ናቸው የሚል መለያየት አይኖርም፤” ትላለች።

የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ወኪል ፓትሪክ ኦኬሎ እንደሚያስረዱት፣ የውኃ ፕሮጀክቱ፣ ስደተኞች እና ተቀባይ ማኅበረሰቦች አብረው በሰላም እንዲኖሩ ከማስቻል ባለፈ፣ የሕዝቡን ጤና እና የኑሮ ኹኔታ በማሻሻል እንዲሁም፣ ኑሯቸውን መገንባት እንዲችሉ በማገዝ ሕይወታቸውን እየለወጠ ነው።

ዩኤንኤችሲአር፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል የገነባው ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው የመጠጥ ውኃ፣ በአካባቢው የሚኖሩ ስደተኞች እና የሚያስተናግዷቸው ማኅበረሰቦች በቀላሉ እንዲጠቀሙት ኾኖ ነው የተሠራው። የኢታንግ ከተማ የውኃ አገልግሎት ፕሮጀክት፣ በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የቆየውን የውኃ እጥረት አስወግዶ ዘላቂነት ያለው የውኃ አቅርቦት እንዲኖር አስችሏል።

ኦኬሎ እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ፣ በሦስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለሚኖሩ ለ230ሺሕ ስደተኞች እና ለ30ሺሕ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ንጹሕ ውኃ በቧንቧ መስመር አማካይነት እያቀረበ ነው፡፡ የሚበዙት የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ስደተኞች ሲኾኑ፣ ሴቶች እና ልጃገረዶችም፣ ውኃ ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝ ሳያስፈልጋቸው፣ በመኖሪያ ቤቶቻቸው ውኃ መቅዳት መቻላቸውን ኦኬሎ አረጋግጠዋል፡፡

ዩኤንኤችሲአር እንደሚለው፣ የውኃ ፕሮጀክቱ፣ በስደተኞች እና በተቀባይ ማኅበረሰቦች መሀከል ያለውን ትስስርም የሚያጠናክር ነው፡፡ በንጽሕና አጠባበቅ እና በውኃ ንጽሕና ላይ የሚሠራው ፕሮጀክቱ፣ በሽታን ለመከላከል እና በተለይ ስደተኞች፣ መደበኛ የውኃ አቅርቦት እንዲያገኙ የሚያስችል የሰብአዊነት ርዳታ አካል ነው።

ሰብአዊ የርዳታ ተቋማት እና የልማት ድርጅቶች፣ እ.አ.አ. በ2014 ደኅንነቱ የተጠበቀ ውኃ ለማቅረብ ሲሉ የጀመሩት ይኸው ፕሮጀክት፣ ከባሮ ወንዝ አጠገብ ከሚገኙ የውኃ ጉድጓዶች የሳበውን ውኃ፣ ወደ ማኅበረሰቡ አቅራቢያ ወደሚገኙ ማጠራቀሚያዎች ያስገባል።

በኢትዮጵያ ስደተኞችን በሚያስተናግዱ ሌሎች አካባቢዎች እና በሌሎች ሀገራትም፣ ፕሮጀክቱን ለመተግበር እና ለማስፋፋት እየተሠራ እንደሚገኝ የዩኤንኤችሲአር የኢትዮጵያ ወኪል ፓትሪክ ኦኬሎ ጠቁመዋል። ኾኖም፣ ከንጹሕ ውኃ በተጨማሪ የሌሎች ሰብአዊ አገልግሎቶች አስፈላጊነትም ተመልክቷል፡፡

ከደቡብ ሱዳን የተሰደደችው ሪቼል፣ የትምህርት አቅርቦትም ቢኖር፣ የስደተኞችን ሕይወት መቀየር እንደሚቻል ትገልጻለች። “የትምህርት ዕድልም ማግኘት ብንችል፣ ለሚያስተናግደን ማኅበረሰብም ይጠቅማል። ለእኛ መተዳደሪያ የሚኾነን ነገር ስናገኝ፣ ለአስጠጋን ማኅበረሰብም ይደርሰዋል፤ ምክንያቱም ተመሳሳይ ችግሮች ነው ያሉብን፤ የሚደርስብንም የኑሮ ጫና ተመሳሳይ ነው፤” በማለት አስረድታለች፡፡ የውኃ ፕሮጀክቱን የሚመሩት የአካባቢው ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ ለእኒኽ ባለሥልጣናት፣ ከሰብአዊ የርዳታ ተቋማት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው እና ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት፣ ተጨማሪ ሰዎችን የመድረስ ዕቅድ መያዙም ተመልክቷል።

XS
SM
MD
LG