በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"በሱዳን የተደቀነው የረሃብ ቸነፈር አደጋ እየተባባሰ ነው" የዓለም የምግብ ፕሮግራም


በምግብ እጦት የሚሰቃዩ ሱዳናውያን ህጻናት በMSF ክሊኒክ እየታከሙ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ፤ በሜቼ ካምፕ፣ ቻድ፣ እአአ ሚያዝያ 6/2024
በምግብ እጦት የሚሰቃዩ ሱዳናውያን ህጻናት በMSF ክሊኒክ እየታከሙ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ፤ በሜቼ ካምፕ፣ ቻድ፣ እአአ ሚያዝያ 6/2024

በጦርነት በተጎዱት የሱዳን አካባቢዎች ቁጥሩ ወደ አምስት ሚሊዮን በሚጠጋ ህዝብ ላይ የተደቀነው የረሃብ ቸነፈር አደጋ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው ሲል የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ። በዚህ ሳምንት ሱዳንን ጎብኝተው የተመለሱት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ካርል ስካዉ ትናንት ረቡዕ ባወጡት መግለጫ የረሃቡ ሁኔታ በፍጥነት እያሽቆለቆለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የከበደ ቸነፈር አፋፍ ላይ ለሚገኘው ህዝብ የሰብዓዊ ረድዔት ተደራሽነትን እናመቻቻለን ብለው ቃል የገቡት ወገኖች በሙሉ አሁኑኑ በተግባር ሊተረጉሙት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ዳርፉር እና ኮርዶፋን አካባቢ የክረምቱ ዝናብ ወቅት ገብቶ መንገዶች ከመዘጋጋታቸው በፊት የምግብ አቅርቦት ለማከማቸት ያለው የጥቂት ሳምንታት ጊዜ ብቻ መሆኑን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለስልጣኑ መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡ ገበሬዎችም ዝናቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ ደህንነታቸው ተጠብቆ የእርሻ መሬታቸው ደርሰው መዝራት እንደሚኖርባቸው አክለዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የውጊያው መቀጠል የድንበር ኬላዎች መዘጋት እና ፍተሻን የመሳሰሉ ችግሮች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ሱዳናውያን እርዳታ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜናዊ ዳርፉር ያለው ሁኔታ ባለፉት ሳምንታት እየተባባሰ መሆኑን ተመድ በማስጠንቀቅ ላይ ነው፡፡ ባለፉት ቀናት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ዋና ከተማዋ ኤል ፋሸር ወደሚገኙት የሱዳን የጦር ሠራዊት ኃይሎች መገስገስ መጀመራቸውን ዘገባዎች አመልክተው ከተማዋ ያሉት ከ8 መቶ ሺህ በላይ ሲቪሎች አደጋ ላይ እንዳሉ ገልጠዋል፡፡

ባለፈው ሰኞ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ተፋላሚዎቹ ወገኖች በአስቸኳይ ውጊያውን አቁመው የተኩስ አቁም ድርድሩን እንዲቀጥሉ ጥሪ አሰምተዋል፡፡

ዳርፉር ውስጥ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ያልተያዘች ከተማ ኤልፋሸር ብቻ ነች፡፡ ኤል ፋሸር ላይ የለየለት ውጊያ ከተቀሰቀሰ እአአ በ2000 ዓም ዳርፉር ውስጥ የአረብ ጃንጃዊድ ታጣቂዎች በዛግዋ፡ ማሳሊት ፡ ፉር እና ሌሎችም አረብ ያልሆኑ ጎሣዎች ላይ የፈጸሙትን የዘር ማጥፋት የመሰለ ጭካኔ የተመላበት ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

ኤል ፋሸር ውስጥ በምግብ ዕጥረት እና በዋጋው ማሻቀብ የተነሳ 330 ሺህ ህዝብ ለከባድ የረሐብ ቀውስ መጋለጡን ተ መ ድ አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG