በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ሱዳን ተዋጊ መሪዎች ላይ ቆንጣጭ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ


ደቡብ ሱዳንን አሁን ወዳለችበት ቀውስና መከራ እንድታሽቆለቁል ምክንያት ሆነዋል ያሏቸው ተፋላሚ ኃይሎች መሪዎች የአሁን ምግባራቸውን እንዲለውጡ ለማስገደድ የሚቆነጥጡ የገንዘብና ሌሎችም እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአጣዳፊ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ላውኮክ ጥሪ አስተላለፉ።

የደቡብ ሱዳን ግጭት አምስተኛ ዓመቱን ቢያስቆጥርም በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን ሕዝቧን ወደተዘፈቀበት እጅግ የከፋ ሥቃይ የሚገፋ ካልሆነ በስተቀር አንዳችም የሚያናፅናና መፍትኄ እየታየ እንዳልሆነ ነው እየተሰማ ያለው።

ብረት አንጋቾቹ አማፂያን ግድያና መድፈርን መሣሪያ አድርገው በሲቪሉ ላይ እያደረሱ ያሉት ሥቃይ ከሸክም በላይ መሆኑን፣ ከአራት ሚሊየን በላይ ደቡብ ሱዳናዊያን ከቤቶቻቸው መፈናቀላቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ብዙ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያወጣቸው ሪፖርቶች እንደሚናገሩት ደግሞ ከሕዝቧ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ቁጥሩ ወደ ሰባት ሚሊየን የሚጠጋ ሰው ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል።

የሰላሙ ሂደት አንዳች ያሳየው ፍሬ አለመኖሩንና ጦርነቱ መቀጠሉን የመንግሥታቱ ድርጅት የአጣዳፊ እርዳታ መርኃግብር አስተባባሪ ማርክ ላውኮክ ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብቶች ጅምላ ረገጣና የሕዝቡ መከራ ማየላቸውን አመልክተዋል።

"የበረቱት ተዋጊዎችና አዋኪዎች - አሉ ላውኮክ - ሰላምንና የሰዉን ደህንነት ከቁብ አይጥፉትም። ጦሩን በሚያዝዙት ሰዎች የገንዘብ ጥቅም ላይ ይበልጥ በቀጥታ ያነጣጠሩ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ሲሉ ላውኮክ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሳስበዋል።

“በሌሎች አካባቢዎች ቪዛ እንዳያገኙ ይደረጋል፤ የተለያዩ የገንዘብ ማዕቀቦች ተጥለዋል፤ የደቡብ ሱዳን የተለያዩ ፓርቲዎች የሃገሪቱን የከርሰ-ምድር ዘይት፣ ወርቅ፣ ዝግባዎቿንና ሌሎችም የተፈጥሮ ኃብቶቿን እራሳቸውን ለማበልፀግ የመጠቀማቸው ነገር ብዙዎችን እያሳሰበ ነው። እጅግ የበዛ የደቡብ ሱዳን ወረት ወደ ውጭ እንዲወጣ መደረጉም የብዙዎች ሥጋት ምክንያት ሆኗል” ብለዋል ላውኮክ።

አንዳንድ መንግሥታት እነዚህን የተደበቁ የሃብት ክምችቶች ምንነትና ምንጭ እንዲፈትሹ የሚያስችሏቸውን ሕጎች እያወጡ መሆናቸውን ሚስተር ላውኮክ አመልክተው ዩናይትድ ስቴትስ ለደቡብ ሱዳን የምትሰጠውን እርዳታ ለመፈተሽ ሰሞኑን መወሰኗ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል። ተመሣሣይ እርምጃም በአውሮፓ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኮሚሽን እየተወሰዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በእርዳታ አቅርቦት ላይ ለውጦችን የማድረግ አስፈላጊነት ግምት ውስጥ ቢገባም ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ሊደርስ የሚገባ እርዳታ ግን እንዲቋረጥ ማንም እንደማይጠይቅ የሚገልፁት የመንግሥታቱ ድርጅት የአጣዳፊ እርዳታ መርኃግብር አስተባባሪ ማርክ ላውኮክ አጣዳፊ ድጋፍ ካልደረሰ ሁኔታዎች ሊባባሱና ብዙ ሰውም ሊሞት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችው በደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለተጨማሪ 45 ቀናት እንዲራዘም የሚጠይቀው ሃሣብ ባለፈው ዓርብ በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ፀድቋል።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

በደቡብ ሱዳን ተዋጊ መሪዎች ላይ ቆንጣጭ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:05 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG