ኰሚሽነር ዛይድ ራዓድ አል-ሁሴን እንዳስረዱት፣ ብዙዎቹ ጥሰቶች የሚፈጸሙት ፖለቲከኞች በሚያካሂዱት ወከባና ግዴለሽነት ነው። ያም፣ ለዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ህግ ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አመልክተዋል። የመብቶች ጥሰትና አለመከበር ዋናው መሠረት፣ ጥላቻ እንደሆነም ኰሚሸሩ ጠቅሰዋል። በገሀድ ለሚፈጸሙ ስቃዮችና የመብት እረገጣዎች፣ ዛሬ ዓለማችን በምስክርነት ትቆማለች በማለት አስረድተዋል።
ትናንት ኦርላንዶ፣ ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኘውና የተመሳሳይ ጾታ ፍቅረኞች በሚያዘወትሩበት የማታ ክበብ ውስጥ በደረሰው የጅምላና የግፍ ጥቃት፣ በእስካሁኑ መረጃ መሠረት ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለው ወደ 53 የሚሆኑ ቆስለዋል።
ይህ ዓይነቱ የጦር መሣሪያ አመጽና ጥቃት እንደሚያሳስባቸውም፣ ኰሚሽነር ዛይድ ተናግረዋል።
ኰሚሽነሩ፣ አንዳንድ አስጊና ችግር ያለባቸው ናቸው የተባሉ አካባቢዎችንም መጠቆማቸው አልቀረም። ሦርያ አንዷ ስትሆን፣ ኢራቅና የመንም አብረው ተጠቅሰዋል። በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪቃ የሚታየውን የመብት እመቃና አመጽ አብረው ያነሱት ኰሚሽነሩ፣ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የስደተኞችና የፍልሰተኞች ሁኔታ መፍትሔ ባለማግኘቱም፣ የአውሮፓ ሕብረትን ከትችት እንደማያድነው አመልክተዋል።
አክራሪ ቡድኖች በማሊ የፈጸሙትን ጥቃት ያወገዙት ኰሚሽነሩ፣ እንደ ቡሩንዲ ያለው ጎሣን ያማከለ ግድያም በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል። አፍሪቃ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ አለመረጋጋትን ሲጠቅሱ፣ ሱዳንን እና ዴሞክራቲክ ኰንጎን በስም ነቅሰው ተናግረዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።