የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘዪድ ራ’አድ አል ሁሴን በቅርቡ ከእሥር ከተፈቱ የመንግሥቱ ተቺዎች፣ የተቃዋሚ ፓርቲና የሃይማኖት መሪዎች፣ የኢንተርኔት አምደኞችና የመብት ጠያቂዎች በአጠቃላይ ወደ ዐስር ከሚጠጉ ሰዎች ጋራ ለአንድ ሰዓት ተወያይተዋል።
በውይይቱም በኢትዮጵያ ይፈፀማሉ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመፈተሽ፣ የደረሰውን ጉዳት ለማረጋገጥ፣ ተጠያቂ አካላትን ለመለየት እንዲሁም በቀጣይ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የማይፈፀምባት ሀገር መሆኗን ለማረጋገጥ በገለልተኛ አካል ምርመራ መደረጉ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን መወያየታቸውን ከተወያዮቹ መካከል ጥቂቶቹ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ዘዪድ ራ’አድ አል ሁሴን በዛሬው ዕለት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ዮናታን ተስፋዬ፣ ሁለቱ የዋልድባ ገዳም መነኮሳት አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም እና አባገብረሥላሴ ወልደሃይማኖት፣ ንግሥት ይርጋ፣ ወይንሸት ሞላ፣ አሕመዲን ጀበልና በፍቃዱ ኃይሉን ማነጋገራቸው ታውቋል። ኮሚሽነሩ ያነጋገሩቸው በተለያየ ጊዜ በእስር ላይ የነበሩና በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ነው።
የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረውን አሕመዲን ጀበልና የኢንተርኔት አምደኛው በፍቃዱ ኃይሉ ስለ ውይይቱ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎቿ፤ በሲቪሎች ላይ በመንግሥቷ በሚካሄድ ሁከቷ፤ የጋዜጠኛነት ነፃነቶችን ማፈኗ፤ በዴሞክራሲያዊ መርኆች ጋር ፊትለፊት በሚጣረስ መንገድ ላይ መቆሟ፤ ሕገመንግሥቷን መጣሷ በብርቱ እንደሚያስወቅሳት የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ያፀደቀው የውሣኔ ሰነድ 128 ያስረዳል።
የፀጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ የሚፈጽሙት ግድያ፣ በእስር ላይ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ የማሰቃየት ተግባራትም መንግሥቱ በእጅጉ የሚተችበት ሌላው ጉዳይ ነው።ይሕም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወቀስበትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በውጭ የገለልተኛ አካላት እንዲጣራ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
በዛሬው ውይይት የተሳተፉት እንደተናገሩት እንደተባለው ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ ጉዳዩን በገለልተኛነት እንዲያጣራ ዕድል ከተሰጠው ጉዳት ያደረሱትን አካላት ለመለየትና ተጠያቂ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ስር ባለች ሀገር ላይ ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ማውራቱ የመብት ጥሰቱን መሸፋፈን መሆኑን በውይይቱ መነሳቱን ጠቁመው፤ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማሳወጅ ምክኒያት ሳይኖር ሕዝብን በዐዋጅ አፍኖ መያዝ በራሱ የመብት ጥሰት እንደሆነ ተገልጿል ብለዋል።
ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘዪድ ራ’አድ አል ሁሴን በተጨማሪም፤ ከአባ ገዳዎች፣ ከጠበቆች፣ ከሰብዓዊ መብት ድርጅት ተወካዮች ጋራ መነጋገራቸው ታውቋል። በመጨረሻም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋራ መነጋገራቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማጠናከር እንዲሁም የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት የሚያስችሉ ለውጦች እየተካሄዱ መሆናቸውን ለኮሚሽነሩ ማብራራታቸው ተዘግቧል።
በውይይቱ ወቅትም ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል ተብሏል።
ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘዪድ ራ’አድ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገላቸው ግብዣ መሠረት ከሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ተገኝተው ውይይቶችን አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ