በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩጋንዳ የኣገር ኣስተዳደር ሚኒስትር ደኤታ፡ ፖሊስ ከልክ ያለፈ ሓይል አልተጠቀመም ሲሉ ተሙዋገቱ


የዩጋንዳ ፖሊሶች በቅርቡ በተቃዋሚ አባላት ላይ የወሰዱት ርምጃ ህገ መንግሥቱን የተከተለ ነው ሲሉ የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ደኤታ ተከላከሉ።

አንዳንዶቹ ተቃዋሚ አባላት ትዕዛዝ አንቀበል በማለታቸው እንጂ ፖሊስ ከልክ ያለፈ ሃይል አልተጠቀመም ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው ጄምስ ባባ ተሙግተዋል።

ዩጋንዳ እኤኣ በመጪው የካቲት 16 ፕሬዚደንታዊና ምክር ቤታዊ ምርጫዎች ታካሂዳለች። ለሰላሣ ዓመታት ያህል ስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቪኒም እንደገና ለመምረጥ ይወዳደራሉ።

በቅርቡ ታዲያ ፖሊስ የተቃዋሚው የዲሞክራሲያዊ ለውጥ መድረክ የፓርቲው መሪ ኪዛ ቢሲጄ ከዋና ከተማዋ ውጭ ሊያደርጉ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ ለመከልከል በወሰደው ርምጃ የፓርቲው አመራር ኣባል የሆኑት ፋቱማ ዜይና አባሊናቦ ልብሳቸው ከላያቸው ተገፎ ራቁታቸውን በቴሌቭዢን ታይተዋል።

የአገር ኣስተዳደር ሚኒስትር ደኤታው ጄምስ ባባ ግን ኣባሊናባዮ ራሳቸው ልብሳቸውን ኣውልቀው ሲያበቁ ፖሊስ ኣወለቀብኝ ብለው ይወነጅላሉ። እንዲያውም የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የFDC ደጋፊዎች ርቃናቸውን መቆም ለፖለቲካ የመጠቀም አዲስ ስልት ጀምረዋል ብለዋል።

ፖሊስ ስርዓት ማስከበር ኣለበት፡ የፖሊስ ትዕዛዝ ኣልቀበል ሲባል ግጭት ሊከሰት ይችላል ያሉት ባለስልጣኑ ያም ሆኖ የተቃዋሚ አመራር አባልዋ ደረሰብኝ ያሉትን በደል የሚመረምር ነጻ ኮሚሽን አቁዋቁመናል ብለዋል። ራሳቸው ተቃዋሚ አባልዋን ከሌሎች የሴቶች ሰብዓዊ መብት ቡድኖች አባላት ጋር በጽህፈት ቤት አነጋግሬቸዋለሁ። የሆነውን አሳይተናቸዋል። ልብሳቸውን ራሳቸው እንዳወለቁ በግልጽ ነው የሚታየው። ነገር ግን እሳቸው የለም ፖሊስ ነው ልብሴን ያወለቀው ብለው አጥብቀው ስለተሙዋገቱ ጉዳዩን የሚመረምር ኣካል፡ ያም ፖሊሶች ሳይሆኑ የሴቶች ድርጅቶች አባላት ያሉበት ኮሚሽን አቁዋቁመናል ሲሉ ባለስልጣኑ አስረድተዋል።

በሂዩማን ራይትስ ዋች መሰረት፡ የዩጋንዳ ፖሊስ በቅርብ ዓመታት በሚከተለው ህግና ስርዓት የማስከበር አሰራር ከባድ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየተፈጸመ ነው። ተቃዋሚዎች በተለይ ከዋና ከተማዋ ከካምፓላ ውጭ ከመራጩ ጋር ለመገናኘት ሲሞክሩ ድብደባ፡ እስር ወይም ከዚያም የከፋ ጥቃት ይደርስባቸዋል ብሉዋል። የዩጋንዳ ፖሊስ በበኩሉ በብሄራዊ የምርጫ ኮምሺኑ የወጣውን ህግና ደምብ ከማስከበር በስተቀር ያጠፋነው የለም በማለት ይከራከራል።

የዩጋንዳ የኣገር ኣስተዳደር ሚኒስትር ደኤታ፡ ፖሊስ ከልክ ያለፈ ሓይል አልተጠቀመም ሲሉ ተሙዋገቱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:15 0:00

XS
SM
MD
LG