በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሱዳናውያን ስደተኞችን በዐማራ ክልል የማዛወር ጥረትን አሜሪካ እንደምትደገፍ ገለጸች


በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ
ሱዳናውያን ስደተኞችን በዐማራ ክልል የማዛወር ጥረትን አሜሪካ እንደምትደገፍ ገለጸች
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:18 0:00

ዩናይትድ ስቴትስ፣ በዐማራ ክልል የሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞችን፣ በክልሉ ወደሚገኝ ወደ ዐዲስ ቦታ ለማዛወር የተጀመረውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሰው ማንኛውንም ጥቃት እንዲቆም አሳስቧል፡፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ ባሉት ሁለት የመንግሥታቱ ድርጅት የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞችን በዞኑ ወደሚገኝ ሌላ ቦታ ለማዛወር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቦታ ማዘጋጀቱን፣ በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት የኩመር፣ የአውላላ እና የዓለምዋጭ መጠለያ ጣቢያዎች አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ ተናግረዋል፡፡

የስደተኞቹ ጉዳይ እንደሚያሳስበው የሚገልጸው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ ላሉ የሱዳን ስደተኞች ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚቀርበው ድጋፍ እጅግ አነስተኛ መኾኑን አመልክቷል፡፡

በዐማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ ሱዳናውያን ስደተኞችን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ በዞኑ ወደሚገኝ ዐዲስ ቦታ ለማዛወር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በምኅጻሩ-ዩኤንኤችሲአር የጀመሩትን ጥረት እንደምትደግፍ ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃለች፡፡

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ የትስስር ገጾቹ ባወጣው መግለጫ፣ “እጅግ ተጋላጭ የኾኑትን የሚያጠቁ ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፤” በማለት፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም አሳስቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር በምኅጻሩ ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር፣ ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ ባወጣው መግለጫ፣ አንድ ሺሕ የሚኾኑ የሱዳን ስደተኞች፣ “የጸጥታ ችግር እና የአገልግሎት እጥረት ገጥሞናል፤” በሚል፣ ከአውላላ እና ከኩመር መጠለያ ጣቢያዎች ለቀው በመውጣት መኖሪያቸውን በጎዳና ዳር ማድረጋቸውን መግለጹ አይዘነጋም፡፡

ስደተኞቹ አለባቸው የተባለውን የደኅንነት ስጋት በተመለከተ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተጠየቁት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ፣ መንግሥት ስጋቱን ለመቅረፍ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረው ነበር፡፡

ቃል አቀባዩ፣ የፌዴራሉ እና የዐማራ ክልል መንግሥታት፣ “የስደተኞቹን ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ እየሠሩ ናቸው፤” ከማለት በቀር፣ ስለ ሥራዎቹ በዝርዝር የገለጹት ነገር የለም፡፡

የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ፣ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሚገኙት የኩመር እና አውላላ መጠለያ ጣቢያዎች ለቀው የወጡት ሱዳናውያን ስደተኞች፣ የደኅንነት ስጋት እና የአገልግሎት እጥረት እንዳለባቸው ገልጸው፣ በዚያው ዞን ውስጥ ወደሚገኝ ሌላ ቦታ ለማዛወር፣ ከዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር ጋራ በመተባበር እየሠራ እንደኾነ ገልጾ ነበር፡፡

ይህ ጥረት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የጠየቅናቸው፣ በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት የኩመር፣ የአውላላ እና የዓለምዋጭ መጠለያ ጣቢያዎች አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ፣ መንግሥት አስፈላጊውን ቦታ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በስፍራው ስላለው የጸጥታ ኹኔታ እና ስደተኞቹን ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር ስለተጀመሩት ተግባራት፣ ስደተኞቹ ከሚገኙበት የምዕራብ ጎንደር ዞን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ስልካቸውን ባለማንሣታቸው ለጊዜው ሊሳካልን አልቻለም፡፡

በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት የኩመር፣ የአውላላ እና የዓለምዋጭ መጠለያ ጣቢያዎች አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ በበኩላቸው፣ በስፍራው ይገኛሉ ያሏቸው የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ጥበቃ በማድረግ ላይ ናቸው፤ ብለዋል፡፡

መንግሥት፣ “የጸጥታ ስጋት አለብን” ያሉ ስደተኞችን ለማዛወር ባዘጋጀው ዐዲስ ቦታ ላይ፣ ስደተኞቹን ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመጀመር የተዘጋጁ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ታምራት፣ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ዩኤንኤችሲአር ግን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዳልገባ አመልክተዋል፡፡

“በዐማራ ክልል የተጠለሉት የሱዳን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበኛል፤” ያለው ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስደተኞች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ከማይቀርብላቸው ሀገራት አንዷ ኾና ቀጥላለች፤ ብሏል፡፡ “በአሁኑ ጊዜ፣ ከሱዳን ለሚጎርፉ ስደተኞች ለጋሾች እየሰጡ ያሉት ሰብአዊ ምላሽ፣ ከሚያስፈልገው መጠን 11 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው፤” ሲልም፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርቱ ስጋቱን ገልጿል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ በዐዲስ አበባው ኤምባሲዋ በኩል ባወጣችው በዛሬው መግለጫ፣ ስደተኞችን ለመርዳት በሚያስፈልገው የገንዘብ ድጋፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት፣ ከአጋሮቿ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋራ ተባብራ እንደምትሠራ አስታውቃለች፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG