የኤክሰን ሞቢል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ሬክስ ቲለርሰን የዲፕሎማሲ ሥራ ልምድ ባይኖራቸውም ከብዙ ሃገሮች ጋር ግን የጠበቀ የንግድ ግንኙነት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር - በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ካቢኔ ውስጥ ቀዳሚው፣ ብርቱው ሥልጣን ነው፤ ከዋይትሃውስ ቀጥሎ፡፡
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀልባቸው የኤክስን ሞቢል መሪ ላይ ከማረፉ በፊት የኒው ዮርክ ከተማ የቀድሞ ከንቲባና በዘመቻቸው ወቅት ግንባር ቀደም ደጋፊያቸው የነበሩትን ሩዲ ጁሊያኒን፣ የዛሬ አራት ዓመት በነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የባራክ ኦባማ ተቀናቃኝ ተፎካካሪና የቀድሞው የማሳቹሴትስ አገረ ገዥ፣ በዘንድሮው የምርጫ ዘመን ደግሞ ዋነኛ ባላንጣቸው የነበሩትን ሚት ራምኒን፣ እንዲሁም የቀድሞውን የአሜሪካ ማዕከላዊ የሥለላ ድርጅት ዳይሬክተርና የጦሩም ጄነራል የነበሩትን ዴቪድ ፔትራያስን አነጋገረዋል፤ ፈትሸዋል፡፡
ሬክስ ቲለርሰን ‘ምናልባት ሳይመረጡ አይቀርም’ የሚል ወሬ የተናፈሰው ባለፈው ሣምንት ውስጥ ነበር፡፡ ቲለርሰን የከትናንት በስቲያው ቅዳሜ ከሚስተር ትራምፕ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ከተገናኙ በኋላ ግን የተመራጩ ፕሬዚዳንት የሸግግር ቡድን ዜናውን ሽው አድርጎ አወጣ፤ ምናልባት መጭው የአሜሪካ የዲፕሎማሲ መሪ እርሳቸው ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ተሰማ፡፡ ያኔ ታድያ ተቺዎች የትራምፕን አዝማሚያ ለመንቀስና ለመንቀፍ ጌዜ አላባከኑም፡፡
እኒህ የነዳጅ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ “የፖለቲካው ዓለም ልምድ የላቸውም” - አንድ መቃወሚያ ነበር፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ግን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የሚፈልጓቸው ሌሎች ችሎታዎች አሉ፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡