የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ለኢየሩሣሌም የእሥራኤል ዋና ከተማ በይፋ እውቅና በመስጠታቸው ከአረቢ ዓለም እንዲሁም ከአውሮፓና ከሌሎችም አካባቢዎች ነቀፋዎችን አስከትሎባቸዋል።
ሚስተር ትረምፕ ትናንት ባደረጉት ንግግር ዩናይትድ ስቴትስ ለእሥራኤል የገባችውን ሃያ ሁለት ዓመታት ያስቆጠረና ከእርሳቸው የቀደሙት ፕሬዚዳንቶች ሁሉ ያልፈፀሙት ቃል እጅግ የዘገየ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ የኢየሩሳሌም ጉዳይ በራሳቸው በእሥራኤላዊያኑና በፍልስጥዔማዊያኑ ድርድር መፈታት ያለበት አወዛጋቢ ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች እንደሚያምኑ ተዘግቧል።
የአሜሪካ-እሥላማዊ ግንኙነቶች ምክር ቤቱ ኒሃድ አዋድ ፕሬዚዳንት ትረምፕ “ሃገራቸው ውስጥና በውጭም የሃይማኖት ፅንፈኝነትን እያበረታቱ ናቸው፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የሰላም ተስፋም የሚገድል ምት አሣርፈውበታል” ብለዋል።
የኢየሩሳሌም ጉዳይ በፍልስጥዔማዊያኑና በእሥራኤል መካከል በሚካሄድ ቀጥተኛ ድርጅር መፈታት ያለበት በመሆኑ እንደሚያምኑ የገለፁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ “ማንኛውም በአንድ ወገን በተናጠል የሚወሰድ እርምጃ የሰላሙን ሂደት ያደናቅፋል” ብለዋል።
ፍልስጥዔማዊው ዋና ተደራዳሪ ሳየብ ኤሬካት በሰጡት መግለጫ “ትረምፕ ዓለምአቀፍ ሕግን፣ ሰብዓዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ጥሰዋል፤ በፍልስጥዔማዊያንና በእሥራኤላዊያን መካከል ያለውን ግጭት ከፖለቲካ ወደ ሃይማኖትዊ ገዳይ እየለወጡት ነው” ብለው የትረምፕ እርምጃ “ዩናይትድ ስቴትስን ከመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ሂደት ተሣታፊነት ውጭ” እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።
ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው ኦርቶዶክስ የአይሁድ ተሟጋች ኅብረት መሪ ናታን ዲያሜንት ለቪኦኤ በስካይፕ በሰጡት ቀል ትረምፕ የኢየሩሳሌምን የእሥራኤል ዋና ከተማነት መወቃቸው “ይልቅ የሰላሙ ሂደት እንዲያንሠራራ ያግዛል” ብለዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ