በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢየሩሳሌም “የእሥራኤል ዋና ከተማ ናት” ሲሉ ፕሬዚዳንት ትረምፕ ዕውቅና ሰጡ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

ፍልስጥዔማዊያኑ “የቁጣ ቀናት” ብለው በጠሯቸው ሦስት ተከታታይ ቀናት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ጥሪዎችን እያስተላለፉ ናቸው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ኢየሩሳሌምን እንደ እሥራኤል ዋና ከተማ በይፋ ዕውቅና ሰጥተው ቴል አቪብ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲም ወደዚያው የማዛወር ዝግጅት እንዲጀመር ትዕዛዝ ሰጡ።

ኢየሩሳሌም የአይሁድ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን እሥራኤል ከተመሠረተችበት (እአአ) ከ1948 ዓ.ም. አንስቶ የመንግሥቷም ዋና መቀመጫ ነው ብለው የሚያምኑት ሚስተር ትረምፕ ይፋ መግለጫቸውን ከመስጠታቸው በፊትም እርምጃው ‘እጅግ ዘግይቷል’ ሲሉ ተናግረዋል።

“የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት (እአአ በ1995 ዓ.ም.) በሁለቱም ፓርቲዎች እንደራሴዎች አብላጫ ድምፅ ያፀደቀውንና ከስድስት ወራት በፊትም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ያሳለፈውን ውሣኔ ተከታታይ ፕሬዚዳንቶች ተግባራዊ ሳያደርጉት ቆይተዋል” ብለዋል።

አረብና የእሥልምና አራማጅ የሆኑ መንግሥታት መሪዎች “አወዛጋቢ ነው” ያሉት ይህ የፕሬዚዳንት ትረምፕ እርምጃ በአካባቢው ውጥረት እንደሚያባብስና እሥራኤልንና በፍልስጥዔማዊያኑን ለማደራደር አሜሪካ የጀመረችውን ጥረት እንደሚያስተጓጉል በመግለፅ ማስጠንቀቂያዎችን ማሰማት ጀምረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ የወሰዱት እርምጃ “ለመካከለኛው ምሥራቅ ሁሉም የሚቀበለው ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ሃገራቸው ያላትን ቁርጠኝነት አያናጋውም” ብለዋል።

ፍልስጥዔማዊያኑ “የቁጣ ቀናት” ብለው በጠሯቸው ሦስት ተከታታይ ቀናት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ጥሪዎችን እያስተላለፉ ናቸው።

ዛሬም በተጠቃውሞ በተጥለቀለቀችው ቤተልሄም ፍልስጥዔማዊያኑ የፕሬዚዳንት ትረምፕን ፎቶዎች ሲያቃጥሉ ታይተዋል።

ኤምባሲው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲዛወር ፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ቢሰጡም ሕንፃው የሚገነባበትን ቦታ ለማግኘትና በጀትም ለመመደብ ጊዜ እንደሚወስድና እስከዚያ ግን ትረምፕ የዝውውሩን ጊዜ እያሸጋገሩ ለመቆየት እንደሚገደዱ ባለሥልጣናቱ አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በአሜሪካ ጥቅሞች ላይ ጥቃቶች ሊሠነዘሩ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ብዙዎች እየገለፁ ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ ስፋት ያላቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እየተደራጁና እየተጠሩም በመሆናቸው የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በአሮጌዪቱ ኢየሩሳሌም፣ በዌስት ባንክ፣ በቤተልሄምና በኢያሪኮ የግል ጉዞዎችንና እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ እዚያ የሚገኘው የአሜሪካ ጠቅላይ ቆንሲል ፅሕፈት ቤት አሳስቧል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG