በውዝግብ ውስጥ ካሉት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች ውስጥ፣ በፓርቲው ሊቀ መንበር ዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ይመራል የተባለው ቡድን፣ የድርጅቱን 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ዛሬ ማክሰኞ ከቀትር በኋላ፣ በመቐለ የሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ ማካሔድ ጀምሯል፡፡
“ጉባኤ ድኅነት” (የመዳን ጉባኤ) በሚል መሪ ቃል በተካሔደው የጉባኤው መክፈቻ ላይ የተናገሩት የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ በፓርቲው ውስጥ “ህወሓትን ለመበተን ዕንቅልፍ ላጣ ቡድን ብቸኛው መፍትሔ ይህ ጉባኤ ነው፤” ብለዋል፡፡
በጉባኤው እንደማይሳተፉ አቋማቸውን ይፋ በማድረግ ሒደቱን የተቃወሙት የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ፣ “በችኮላ እና የጋራ መግባባት ሳይደረስበት” የተጠራ ነው፤ ያሉት የዛሬው ጉባኤ፣ “ይቃወሙናል የሚሏቸውን የተወሰኑ አመራሮች ለማስወገድ በማለም የሚካሔድ እንደኾነና ትግራይን አደጋ የሚጥል ነው፤” ብለውታል፡፡
በፓርቲው ስለተጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ከብዙኀን መገናኛ ዘገባ መረዳቱን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ጠቅላላ ጉባኤው፣ አስፈላጊ የኾኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ያልተሟሉበትና የቦርዱ ታዛቢዎች ያልተገኙበት በመኾኑ ሊካሔድ እንደማይችል፣ ትላንት ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ አስጠንቅቋል፡፡ ጉባኤው ከዚኽ የቦርዱ ውሳኔው ውጭ ከተካሔደም፣ ለጉባኤው እና በጉባኤው ላይ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች በሙሉ እውቅና እንደማይሰጥ አስታውቋል፡፡
መድረክ / ፎረም