የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ምክትል ሊቀ መንበርን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንደማይሳተፉ የገለጹበት 14ኛው የፓርቲው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ነገ ማክሰኞ፣ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በመቐለ የሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ እንደሚጀምር፣ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት እና የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ገልጿል፡፡
ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤው፣ “ጉባኤ ድኅነት” (የመዳን ጉባኤ) ተብሎ መሰየሙን፣ ፓርቲው በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ትላንት እሑድ፣ ነሓሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ለብዙኀን መገናኛ በሰጡት መግለጫ፣ “ትልቅ ብልሽት ውስጥ ያለውን የህወሓት አመራር በማስተካከል ፓርቲውን ለማዳንና ሕዝቡ እንዲክስ ለማድረግ ጉባኤው አስፈላጊ ነው፤” ብለዋል፡፡
“የፓርቲው ትልቁ ብልሽት ያለው በአመራሩ ውስጥ ነው፡፡” ያሉት ዶ.ር ደብረጽዮን “አንድ ላይ መሰማራት የማይችል ፓርቲ እየኾነ ነው፡፡ ስለዚኽ፣ ወደ ጉባኤ ከሚያስገቡን መነሻዎች አንዱ አመራሩን የማስተካከል አስፈላጊነት ነው፡፡ ለዚኹ ብቻ ተብሎ ጉባኤ ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከአሁን በፊት የተካሔደውን ጉባኤ ተከትሎ የተፈጸሙ ሥራዎች አሉ፤ እነርሱም ተገምግመዋል፡፡ ‘የመመከት ሒደት’ን ጨምሮ በሥራ አስፈጻሚ እና በማዕከላዊ ኮሚቴ ፖለቲካዊ ግምገማ አካሒደን ጨርሰናል፡፡ ይኸው ግምገማ ውሳኔ የሚያገኘው ደግሞ በጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡” ብለዋል።
ዶር. ደብረ ጽዮን በመግለጫቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለህወሓት የሰጠው በልዩ ኹኔታ የመመዝገብ ውሳኔ፣ “ከፓርቲው ጥያቄ ውጭ ነው፤” ብለዋል፡፡ ይህ ውሳኔ፣ የኀምሳ ዓመት ዕድሜ ያለውን ህወሓትን ነሐሴ 3 ቀን እንደተመሠረተ የሚያስመስለውና ከዚያ በፊት የተፈረመውን የፕሪቶሪያን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነትም “የለም” እንደማለት የሚያስቆጥር ነው፤ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ጥያቄአቸውን በፖለቲካዊ መንገድ እንደሚቀጥሉ ሊቀ መንበሩ ገልጸው፣ በዚኽ ሒደትም ፓርቲው ውስጡን ለማጽዳት ጉባኤውን እንደሚያካሒድ አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ጽሕፈት ቤት፣ ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ የህወሓትን የሕግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ፣ መንግሥት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ውስጥ “የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ አልነበረም፤” በማለት፣ የፌደራል መንግሥቱ ከግማሽ ርቀት በላይ ተጉዞ፣ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ከሚጠበቅበትና ካለበት ግዴታ አልፎ ከምርጫ ቦርድ እና ከህወሓት ጋራ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ውይይቶችን ማድረጉን አስታውሷል፡፡
ህወሓትም፣ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ሥልጣን የማክበር ግዴታ ገብቷል፤ ያለው መግለጫው፣ ፓርቲው፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ ሕግ እና የምርጫ ቦርድን ሥልጣን በማክበር የመሥራት ግዴታ እንዳለበት አሳስቧል።
ህወሓት በኀይል እና በዐመፅ እንቅስቃሴ በመሳተፉ የፓርቲው ምዝገባ ተሰርዞ ሕጋዊ ሰውነቱን ያጣው በምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፣ ሰላምን የማጽናት አስፈላጊነትን ባገናዘበ መልኩ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት፣ ህወሓትም ኾነ ሌሎች የትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቡድኖች ወደ ሕጋዊ መሥመር ሊመጡ የሚችሉበት የሕግ ማሻሻያ መደረጉን ገልጿል፡፡
በተሻሻለው የዐዋጁ ድንጋጌ መሠረት፣ የሰላም ስምምነት መፈጸሙን አስመልክቶ የፍትሕ ሚኒስቴር ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና እንዲኖረው የትብብር ጥያቄ አቅርቧል፤ ያለው መግለጫው፣ ህወሓትም የሚጠበቅበትን የፓርቲ ሰነዶች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቦ በተሻሻለው ዐዋጅ መሠረት ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት ማግኘቱን አስረድቷል፡፡
ስለኾነም፣ የምዝገባ እና የሕጋዊ ሰውነትን ጉዳይ በዚኹ መቋጨት እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ላይ ያመለከተው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት፣ “አላስፈላጊ እና ሕዝብን የማይጠቅም ትርጉም አልባ ንትርክ አስወግደን፣ የኹሉም አካላት ርብርብ ሰላምን በማጽናት፣ በመልሶ ግንባታ እና በልማት አጀንዳ ላይ ሊኾን ይገባል፤” ብሏል፡፡
በአንጻሩ፣ የጉባኤው ቅድመ ዝግጅት ሒደት፥ “ማዕከላዊ ኮሚቴው ያልተግባባበት፣ የፓርቲው ቁጥጥር ኮሚሽን ያልተቀበለውና ከህወሓት አሠራር ውጭ የተዘጋጀ ነው፤” ያሉት የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር እና የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ “ህወሓትን በሚያፈርስ ጉባኤ ላይ አንሳተፍም፤” ሲሉ ባወጡት መግለጫ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡
እነአቶ ጌታቸው በዚሁ የጽሑፍ መግለጫቸው፣ “ከአሠራር ውጭ” ሲሉ የኮነኑትን የጉባኤ ዝግጅት የሚያካሒደው “ማዕከሉን በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ያደረገ ቡድን ነው፤” ሲሉ ከሰዋል፡፡
የጉባኤውን ተሳታፊዎች ውክልና በተመለከተም፥ “በትግራይ ክልል በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ ዞኖች ባሉ ተወካዮች ተቀባይነትን ያላገኘ፣ እንዲሁም የምዕራብ ትግራይን፣ ከፊል ምሥራቃዊ ዞንና የፀለምቲ አካባቢን ያላሳተፈ እና ተሳታፊዎችን ወክለዋል በተባሉ አካባቢዎችም ተረጋግቶ ምርጫ ያልተካሔደበት ነው፤” ብለዋል፡፡
አያይዘውም፣ “ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መግባባት ያልተደረሰበት፣ ለተወሰነ ቡድን ጥቅም ሲባል እየተካሔደ ያለ” በማለት ያጣጣሉት እነአቶ ጌታቸው፣ “የትግራይ ሕዝብንና ፓርቲያችን ህወሓትን ወደተወሳሰበ ችግር በሚያስገባ ጉባኤ ላይ አንሳተፍም፤” ብለዋል፡፡
“ጉባኤውን ተከትሎ ለሚመጣ ችግር ተጠያቂው ቡድኑ ነው፤” ያሉት ተቃዋሚ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ፣ “ይህንንም እንታገለዋለን” ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ፣ ራሱን ከድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤው ማግለሉን ያስታወቀው የህወሓት ቁጥጥር ኮምሽንም፣ ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ “ጉባኤው፣ በእልክ እና በማንአለብኝነት ለአንድ ቡድን ፍላጎት ለማካሔድ ዝግጅት እየተደረገበት ያለ ነው፤” ሲል ወንጅሏል፡፡
ኮሚሽኑ ያቀረባቸውን የመተማመኛ ሓሳቦች ወደ ጎን በመተው የሚካሔድ የጉባኤው ዝግጅት እንደኾነ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ “ፓርቲውን የሚበትን፣ የትግራይ ሕዝብን አንድነትም የሚያፈርስ ነው፤” በማለት ተቃውሟል፡፡
ትላንት እሑድ ለክልሉ ብዙኀን መገናኛ መግለጫ የሰጡት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው፣ “በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ልዩነት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ ይፈታል፤” ካሉ በኋላ፣ በክልሉ በተለይ በመቐለ ከተማ፣ የድጋፍም ኾነ የታቃውሞ ሰልፍ ለተወሰነ ጊዜ የተከለከለ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
የህወሓት ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባኤ እና ሌሎች በክልሉ የሚከናወኑ ዓመታዊ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ፣ የክልሉ የጸጥታ ኀይል ዝግጅት ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
አክለውም “ከዚሁ የህወሓት ጉባኤ ጋራ ተያይዞ፣ በድጋፍም ኾነ በተቃውሞ የሚካሔድ ሰልፍ አይፈቀድም፡፡ በተለይ በአደባባይ የሚከበረው የአሸንዳ በዓል በመኖሩ፣ በመቐለ እና አካባቢዋ የኾነ መፈክር በመያዝ የፖለቲካዊ ድጋፍም ኾነ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሔድ ለተወሰነ ጊዜ አንፈቅድም፡፡” ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው፣ በህወሓት ፖለቲካዊ አመራር ውስጥ ባለው ልዩነት፣ የክልሉ የጸጥታ ኀይል፣ ለየትኛውም አካል ውግንና አያሳያም፤ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋራ በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ለፓርቲው በጻፈውና፣ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ደብዳቤ፣ ህወሓት ከቦርዱ እውቅና ውጪ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ እንደማይችል ገልጿል።
ህወሓት ከቦርዱ እውቅና ውጭ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ከብዙኃን መገናኛ መስማቱን በመግለጫው የጠቀሰው ቦርዱ፣ አካሄዱ ትክልል እንዳልኾን በመግለጽ አሳስቧል።
ቦርዱ፣ አንድ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ አስፈላጊ የኾኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እንዲያውቅ ባልተደረገበት፣ ባልተከታተለው እና ባላረጋገጠበት እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ያልተገኙበት ተጠራ የተባለ ጉባኤ መካሄድ እንደማይችል በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።
ተጠራ የተባለው ጉባኤ ከተካሄደም፣ በጉባኤ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና እንደማይሰጥ አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም