ምግብ እና ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶች የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች በአፋር ክልል በኩል ያለምንም ችግር እንዲተላለፉ መንግሥት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን አስታውቋል፡፡ “መንግሥት ሆን ብሎ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዳይገባ አድርጓል" በሚል በህወሓት ተደጋጋሚ ክስ ቢቀርብም፣ መንግሥት በበኩሉ ተጠያቂው ህወሓት መሆኑን መግለጹ ይታወቃል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ከሦስት ቀናት በፊት ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል የውጭ ግኙነት ጽሕፈት ቤቱ ከፍተኛ አመራር የሆኑትን ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወትን ላለፉት ሦስት ወራት ወደ ትግራይ ክልል የገባ የእርዳታ እህል የጫነ መኪና እንደሌለ መናገራቸው ይታወሳል።
በሌላ ዜና የዓለም ጤና ድርጅት መድኃኒት እና ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ ክልሉ ለማስገባት ላቀረበው ጥያቄ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ እንዳልተሰጠው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገልፀዋል።
የዶ/ር ቴድሮስን ክስ ያጣጣሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው “ከህወሓት ጋር ባላቸው የፖለቲካ ግንኙነት በመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት ነው” ብለዋል፡፡