በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የታዳጊ ወጣቶች ህይወት ያለፈበት የደቡብ አፍሪካው መጠጥ ቤት ባለቤት ክስ ይከሰሳሉ ተባለ


ደቡብ አፍሪካ በሚገኝ የምሽት ክበብ ውስጥ የሞቱ ሰዎች አስከሬን ወደ መኪና ሲጫን ምስራቅ ለንደን፣ ደቡብ አፍሪካ እአአ ሰኔ 26/2022
ደቡብ አፍሪካ በሚገኝ የምሽት ክበብ ውስጥ የሞቱ ሰዎች አስከሬን ወደ መኪና ሲጫን ምስራቅ ለንደን፣ ደቡብ አፍሪካ እአአ ሰኔ 26/2022

ትናንት በደቡብ አፍሪካ ምስራቅ ኬፕ ክፍለ ግዛት በሚገኝ ቡና ቤት ቢያንስ አስራ ሰባት ወጣቶች ህይወታቸው አልፎ የተገኙ ሲሆን ሌሎች አራት ወጣቶች ደግሞ ህክምና ላይ ሳሉ ሞተዋል።

ወጣቶቹ ህይወታቸው ያለፈበት ምክንያት እየተመረመረ ሲሆን የቡና ቤቱ ባለቤት ክስ እንደሚጠብቃቸው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ዕሁድ ንጋት ላይ ቡና ቤቱ ውስጥ ህይወታቸው አልፎ የተገኙት ታዳጊ ወጣቶች አስከሬን ላይ ምንም ዓይነት የጉዳት ምልክት እንዳልታየ የገለጹት ጉዳዩን እየመረመሩ ያሉት ፖሊሶች ተመርዘውም ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።

የቡና ቤቱ ባለቤት ሲያካንጄላ ኢንዴቩ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል በሰጡት ቃል ቡና ቤቱ ከሞላ በኋላ በግድ ተጋፍተው ሊገቡ የሞከሩ ወጣቶች ነበሩ ብለዋል። መርማሪዎች ግን በሞቱት ወጣቶች ሰውነት ላይ ምንም ዓይነት ከግፊያ ጋር የተያያዘ ጉዳት ምልክት የለም በማለት የመጠጥ ቤቱ ባለቤት የሰጡት ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል። ከሞቱት መካከል የአስራ ሦስት ዓመት ታዳጊዎችም እንዳሉባቸው መርማሪዎቹ ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፖሳ ለሞቱት ወጣቶች ቤተሰቦች ሀዘናቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል።

በሀገሪቱ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች መስጠት በህግ የተከለከለ ሆኖ ሳለ ታዳጊዎች ቡና ቤቱ ሊገቡ እንዴት እንደቻሉ ፕሬዚዳንቱን እንዳሳሰባቸው ቃል አቀባያቸው ገልጸው ህጉ በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ተገቢው ዕርምጃ እንዲወስድ ፕሬዚዳንቱ የሚፈልጉ መሆኑን አክለው አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG