በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካን የዛሬ ሁኔታ የሚዳስሰው የባይደን ዓመታዊ ንግግር


ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከጦርነት እስከ ኢኮኖሚ የሚዳስስሰውን “ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን” ንግግራቸውን የካቲት 28/2016 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ፊት ሲያቀርቡ።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከጦርነት እስከ ኢኮኖሚ የሚዳስስሰውን “ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን” ንግግራቸውን የካቲት 28/2016 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ፊት ሲያቀርቡ።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከጦርነት እስከ ኢኮኖሚ የሚዳስስሰውን “ዘ ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን” ንግግራቸውን የጀመሩት "በሃገር ውስጥም በውጭም ዴሞክራሲና ነፃነት አደጋ ላይ ወድቀዋል" በሚል መልዕክት ነው። ፕሬዚዳንቱ ለዚህ መልዕክታቸው መንደርደሪያ እንዲሆንም ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዘቬልት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ ለኮንግረሱ አሰምተው የነበረውን ተመሣሣይ መልዕክት አስታውሰዋል።

የዛሬውን መልዕክታቸውን የሚያሰሙትም እንደፍራንክሊን ሁሉ ኅብረቱን ለማንቃት እንደሆነ አመልክተዋል። በውጭ አለ ያሉትን አደጋ ሲናገሩም “የሩሲያው ፕሬዚዳንት ዩክሬንን አያቆሙም። ዩክሬን ግን እየጠየቁን ያለውን ትጥቅ ከሰጠናቸው ፑቲንን ይቆማሉ” ብለዋል።

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ትረምፕ ላይ ብርቱ ወቀሳ ሠንዝረዋል። ሮናልድ ሬጋን ለያኔው የሶቪየት ሕብረት ፕሬዚዳንት ሚኻይል ጋርባቾቭ የበርሊንን ግንብ እንዲፈርሱ ጠይቀው እንደነበር አስታውሰው "ትረምፕ ግን ፑቲን የፈለጉትን እንዲያደርጉ እንደሚያበረታቱ ተናግረዋል" ብለዋል።"ይህ ጨርሶ ተቀባይነት የለውም" ያሉት ባይደን "ሃገርህን መወደድ ያለብህ ስታሸንፍ ብቻ አይደለም" ሲሉ አክለው። ኔቶን የበለጠ ጠንካራ እንደሚያደርጉ ፕሬዚዳንት ባይደን አመልክተው በአዳራሹ ውስጥ በእንግድነት የተገኙትን ኔቶን ሰሞኑን የተቀላቀለችውን የስዊድንን ጠቅላይ ሚኒስትር አስነስተው እንኳን ደኅና መጡ ብለዋቸዋል።

ጆ ባይደን በዕለቱ በእንግድነት የተገኙትን ኔቶን ሰሞኑን የተቀላቀለችውን የስዊድንን ጠቅላይ ሚኒስትር አስነስተው እንኳን ደኅና መጡ ሲሏቸውና ባለቤታቸው ጂል ባይደን ንግግሩን በጭብጨባ ሲያጅቡ።
ጆ ባይደን በዕለቱ በእንግድነት የተገኙትን ኔቶን ሰሞኑን የተቀላቀለችውን የስዊድንን ጠቅላይ ሚኒስትር አስነስተው እንኳን ደኅና መጡ ሲሏቸውና ባለቤታቸው ጂል ባይደን ንግግሩን በጭብጨባ ሲያጅቡ።

ፕሬዚዳንት ባይደን በተጨማሪም የእርሳቸው ተቀናቃኝ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፅንስን በማቋረጥ ላይ ያላቸውን አቋም በብርቱ ነቅፈው አውግዘዋል። አሜሪካውያን ለመድሃኒት እና ለህክምና የሚያወጡት ወጪ እንደሚያስቀንሱ ፕሬዚደንቱ ቃል ገብተዋል። በዚህም 200 ቢሊዮን ዶላር እንድሚያድኑ ተናግረዋል። ለሁሉም ዜጎች የመድሃኒትን ዋጋ 40 በመቶ እናስቀንሳለን፣ የኦባማ የጤና ዋስትና አሁንም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

“ይህንን የጤና ዋስትና ተቃዋሚዎቻችን ሊሰርዙት ይፈልጋሉ፣ ያንን አንፈቅድም!” ሲሉ ተናግረዋል። በቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን የሚመራና በሴቶች ጤና ምርምር ላይ የሚያተኩር ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ትኩረት ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ የሃገሪቱ በጀት ክፍተት ጉዳይና የግዙፍ ኮርፖሬቶችን የታክስ ክፍያ ይገኝበታል። እስካሁን በነበረው ጊዜ የአንድ ትሪልዮን ዶላር የታክስ ክፍተት ማጥበብ መቻላቸውን ተናገረው ግዙፎቹ ኮርፖሬሽኖች የሚገባቸውን እንዲከፍሉ በማድረግ የተጨማሪ 3 ትሪልዮን ዶላር ለመዝጋት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

"እኔ ካፒታሊስት ነኝ" ያሉት ባይደን "አንድ ሚልዮን ዶላር ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ መልካም፤ የድርሻህን ግን መክፈል ይገባሃል ብለዋል። በእርሣቸው አስተዳደር በዓመት ከ400 ሺህ በታች የሚያገኝ ማንም ሰው የታክስ ጭማሪ እንደማይደረግበት አስታውቀዋል።

የፕሬዚደንት ጆ ባይደን የአሜሪካ የዛሬ ሁኔታ /ዘ ስቴት ኦፍ ዘ/ ዩኒየን ንግግር
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:25 0:00

ድምፅ የመስጠት መብትን ጉዳይም አንስተው ተወካዮቹ በእንደራሴ ጃን ሉዊስ የተረቀቀውን የመምረጥ ነፃነት ህግ እንዲያፀድቁ ጠይቀዋል። ድምፅ የመስጠት መብትን ታሪክ ከሃገሪቱ የዘር መድልዎ ጊዜ አንስቶ የነበረውን ዳራ ተርከዋል።

መሠረታዊ ነፃነቶችን እንደሚጠብቁ ፕሬዚዳንቱ አመልክጠው የፆታ ሽግግር ያደረጉ አሜሪካዊያንን የእኩልነት መብቶች ለማስጠበቅ የቀረበውን የህግ ረቂቅ እንዲያፀድቁ ጠይቀዋል። የሠራተኞች መብቶች እንዲጠበቁ፣ የደመወዝ ዝቅተኛ ወለል ከፍ እንዲል ጠይቀዋል።

“በሁለቱም ፓርቲዎች ካለፈው ህዳር ጀምሮ ስንደራደርበት የቆየነው ፍልሰተኞችን የተመለከተው ረቂቅ ሕግ፣ 1ሺሕ 500 የድንበር ጠባቂዎችን ሊያስቀጥር እና 100 የሚሆን ተጨማሪ የፍለሰተኛ ሕግ ዳኞችን ቀጥሮ፣ በሂደት ላይ ያሉትን 2 ሚሊዮን የፍ/ ቤት ጉዳዮች እንዲይዙ ያደርግ ነበር። 4ሺሕ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ጉዳይ የሚመለከቱ ሠራተኞች እንቀጥር ነበር።” ሲሉ ፍልሰተኞችን በተመለከተ በንግግራቸውን ማብራሪያ የሰጡት ባይደን፤ “ረቂቅ ሕጉ ሕይወትን ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ በድንበራችንም ላይ ስር ዓት እንዲሰፍን ያደርግ ነበር።” ብለዋል።

የዴሞክራት ተወካዮች ለሴቶች መብት ትኩረት ለመስጠት ነጭ በንግግሩ ላይ ታድመዋል።
የዴሞክራት ተወካዮች ለሴቶች መብት ትኩረት ለመስጠት ነጭ በንግግሩ ላይ ታድመዋል።

ሕጉ ግን በፖለቲካ ምክኒያት መጽደቅ እንዳልቻለ ጠቁመው፤ “የሪፐብሊካን ጓዶቼ የፍልሰተኛ ረቂቅ ሕጉን ለአሜርካ ሕዝብ ስትሉ አጽድቁ።” ሲሉ ጠይቀዋል።

“ከኔ ቀደም ብለው ፕሬዝደንት የነበሩት እየተመለከቱን ከሆነ፣ ፖለቲካ ከመጫወትና የም/ቤት አባላት ሕጉን እንዳያጽድቁ ጫና ከማሳደር ይልቅ፣ ኮንግረስ እንዲያጽድቅ ያድርጉ።” ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ታሪክ እንሥራ ያሉት ባይደን በመጭዎቹ ስድሥት ዓመታት ውስጥ የተቃጠለ ጋዝ ልቀትን በግማሽ የመቀነስ ቁርጠኛነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ለህዝብ ደኅንነት ጥበቃ ግዙፍ ትኩረትና ነዋይ ማዋላቸውን ባይደን ተናግረዋል። እርሣቸው ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ወንጀል በመላ ሃገሪቱ በ30 ከመቶ አሻቅቦ እንደነበረ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱንና በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 50 ከመቶ መውረዱንም ገልፀዋል።

በሰው ዘንድ መተማመን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በቤት ውስጥ የሚፈጠሩ የሁከት አድራጎቶችን ለመግታት እንደሚጥሩ፣ የሴቶችን ደኅንነትን ለመጠበቅ ፌደራል ህግ ማስከበርን እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል።

ባለ ከፍተኛ ካሊበር የጥቃት መሣሪዎችን ለማገድ እንደሚንቀሳቀሱን የመሣሪያ ገዥዎች ማንነት እንዲመረመርም ለማደረግ እንደሚጥሩ አስታውቀዋል።

አገራቸውን በአገር ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶች እየተጋፈጠች ባለችበት ወቅት መካከለኛው ምስራቅን ጨምሮ በውጭ ያሉ ቀውሶችንም ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

የእስራኤልን እና የፍልስጤምን ጉዳይ በዳሰሱበት ንግግራቸው “ባለፉት አምስት ወራት ያየነው፣ ልብ ያሚያደማ ነገር ነው። ለእስራኤሎችም፣ ለፍልስጤማውያንም እንዲሁም በዚህ በአሜሪካ ለሚገኙ በርካታ ሰዎች የሚያሳዝን ጉዳይ ነው፡፡ ቀውሱ የጀመረው ሐማስ ጭፍጨፋ በመፈጸሙ ነው። 1ሺሕ 200 ሰዎች ታረዱ። በርካቶች የጾታ ጥቃት ተፈጸመባቸው።” ብለዋል።

“በአይሁዶች ላይ ከተፈጸመው ጭፍጨፋ ወዲህ የከፋ ሞት የታየበት ነው።” ያሉት ባይደን “250 የሚሆኑ ታግተው ተወስደዋል። በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው ይገኛሉ። ለሁሉም ቤተሰቦች ቃል የምገባው፣ ታጋቾች እስከሚለቀቁ እረፍት አንደማንወስድ ነው።” ብለዋል።

“ከ30 ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። አብዛኞቹ ሐማሶች አይደሉም። በሺህ የሚቆጠሩት ምንም ያላጠፉ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው። ልጆች ካለ ወላጅ ቀርተዋል።ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ላይ ናቸው ወይም ተፈናቅለዋል።” ሲሉም አክለዋል።

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ንግግራቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው የአላባማ እንደራሴ ኬቲ ብሪት ምላሽ ሰጥተዋል።

ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ንግግራቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው የአላባማ እንደራሴ ኬቲ ብሪት ምላሽ ሲሰጡ።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ንግግራቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው የአላባማ እንደራሴ ኬቲ ብሪት ምላሽ ሲሰጡ።

“በፕሬዚዳንት ባይደን ጊዜ የሃገራችን ደኅንነት ዝቅ ብሏል” ብሏል ያሉት ሴናተር ብሪት። “የአሜሪካ ህልም ወደ አስፈሪ ቅዠትነት ተቀይሯል” ብለዋል። የሃገሪቱ ሁኔታ “የተዳከመ ነው” ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ሴናተር ብሪት በተለይ በደቡብ ድንበር አካባቢ ላለው ሁኔታ ሰፋ ያለ ትኩረት ሰጥተዋል። ባይደን የተረከቡት “እጅግ ጠንካራ ድንበር ነበር” ያሉት ብሪት ባይደን አውጥተዋቸዋል ባሏቸው 94 ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዞች አሁን አለ ያሉትን “አደጋ ጋብዘዋል” ብለዋል። “የባይደን የድንበር ፖሊሲ አሳፋሪ ነው” ሲሉ አክለዋል። “የአደገኛና አደንዛዥ ቅመሞችና መድሃኒቶች መስፋፋት፣ የዕፅና ወንጀል ቡድኖች ግድያ መበራከት የባይደን ፖሊሲ ወጤት ናቸው” ብለዋል።

“ኢኮኖሚው ለአሜሪካውያን ከብዷል። አሜሪካውያን ከፍተኛ የባንክ ዕዳ አለባቸው። የገንዘባችን የመግዛት አቅም ተዳክሟል።

በመካከለኛው ምሥራቅ አሜሪካውያን በጥቃት ላይ ናቸው። ፕሬዝደንት ባይደን አመራር እየሰጡ አይደለም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።

“አሜሪካውያን ራሳችሁን ጠይቁ፣ ከሦስት ዓመት በፊት ከነበራችሁበት የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ናችሁ? አሜሪካ ከዚህ በፊትም ተፈትና ነበር። በታሪክ የነበሩት ትውልዶች ፈተናቸውን አሸንፈዋል። ይህ ትውልድም ፈተናዎችን አሸንፎ ይወጣል።”

ብለዋል ሴናተር ኬቲ ብሪት ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን "የኅብረቱ የዛሬ ሁኔታ" ዓመታዊ ሪፖርትና መልክዕክት በሰጡት የሪፓብሊካን ምላሽ። የ42 ዓመት ዕድሜዋና እጅግ ወጣቷ ሪፓብሊካን የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ኬቲ ብሪት ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ "ሃገራችን አሁን በዚህ ሁኔታ ላይ ብትሆንም እጅግ የተሻሉ ቀናት ግን ይመጣሉ" ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG