ፑንትላንድ እና ሶማሌላንድ በግዛቶቻቸው የሚገኙትን ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችን እንዲዘጉ የተሰጠውን ትዕዛዝ እንደማይቀበሉ ዛሬ አስታወቁ።
ሶማሊያ፣ በሞቃዲሾ የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሀገር ለቀው እንዲወጡ ማዘዟን፣ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ትላንት ኀሙስ፣ መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ኢትዮጵያ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን በመግለፅ ክስ ያሰማው የሶማሊያ መንግሥት፤ ሞቃዲሾ የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር በ72 ሰአት ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መጠየቋን እና አዲስ አበባ ያሉትን አምባሳደሯንም መጥራቷን ትናንት አስታውቃ ነበር።
በተመሳሳይም ከሶማሊያ የተገነጠለችውን የሶማሊላንድ ግዛት እና ከፊል ራስ ገዟን ፑንትላንድ በዚያ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤቶች በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲዘጉ አዛለች።
ይሁንና ሶማሌላንድ በዋና ከተማዋ ሀርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት እንዲዘጋ ሞቃዲሾ ያቀረበችውን ጥያቄ የሶማሌ ፌደራል መንግሥት እንደዚያ ያለ ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ ውድቅ አድርጋለች።
ሶማሊያ ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር ወር ከሶማሌላንድ ጋራ የተፈራረመችውን የባህር በር የተመለከተ ስምምነት፣ “ህገ-ወጥ” እና ሉአላዊነቴን የጣሰ ነው ስትል ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቷም ይታወቃል።
መድረክ / ፎረም