በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሃገሯ አስወጣች


አምባሳደር ሙክታር፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሙሐመድ
አምባሳደር ሙክታር፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሙሐመድ

ሶማሊያ ዛሬ ሐሙስ በሞቃዲሹ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ከሃገሯ እንዲወጡ አድርጋ፣ በራስ ገዟ ፑንትላንድ እና በተገነጠለችው ሶማሊላንድ የሚገኙ ሁለት የቆንስላ ጽ/ቤቶችን ዘግታለች፡፡

የሶማሊያ የዛሬው ውሳኔ የመጣው፣ በሶማሊላንድ የገንዘብ ሚኒስትር የተመራ የልዑካን ቡድን ትናንት ረቡዕ በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ማድረጉን ተከትሎ ነው። ሁለቱ ወገኖች በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የኃይል ማመንጫ እንዲሁም በሌሎች የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ እንደተነጋገሩ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ካወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር በሊዝ እንድታገኝ የሚያስችላት ነው የተባለ የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋራ ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ መፈራረሟን ተከትሎ፣ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል ውጥረት ተከስቷል።

ሶማሊላንድ ከእ.አ.አ 1991 ዓ.ም. ጀምሮ በራስ ገዝነት ብትቆይም፣ ሶማሊያ አሁንም እንደ ግዛት አካሏ ስለምትመለከታት፣ ከኢትዮጵያ ጋራ ስምምነት መፍጠሯ አስቆጥቷታል። ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ፣ ሶማሊያ “ራሷን ትከላከላለች” ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ ተናግረዋል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሃገሯ ማባረሯ፣ አል ሻባብን ለመፋለም በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ልዑክ ሥር የተሰማሩት 3ሺሕ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ዕጣ ምን ይሆናል የሚል አሳሳቢ ሁኔታን ፈጥሯል።

ወታደሮቹን የማስወጣት ሃሳብ እንደሌላቸው የሶማሊያው ፕሬዚደንት ባለፈው የካቲት መናገራቸውን የሮይተርስ ዘገባ አስታውሷል።

በሌላ በኩል፣ የሶማሊያ ፓርላማ ‘አንድ ሰው አንድ ድምጽ’ የሚለውን ዓለም አቀፍ የምርጫ መርህ እንደሚከተልና ሕገ መግስቱንም ማሻሻሉን ባለፈው ሳምንት ማስታወቁን ተከትሎ፣ ራስ ገዟ ፑንትላንድ ለፌደራል ተቋማት እውቅና እንደማትሰጥ አስታውቃለች።

“በጋራ መግባባት ላይ የሚደረስበት ሕገ መንግሥታዊ ሂደት እስከሚፈጠር ድረስ የፑንትላንድ አስተዳደር ለፌዴራል ተቋማት እውቅና አይሰጥም፣ ተቋማቱ ላይም እምነት የለውም” ብላለች ሶማሊላንድ ባለፈው እሁድ ባወጣችው መግለጫ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG