የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ በኤርትራ የነበራቸውን የሁለት ቀናት ጉብኝት አጠናቀዋል።
ሶማሊያ የተረጋጋች መሆኗን ማረጋገጥ የቀጠናውን ሠላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የሁለቱ ሃገራት ፕሬዝደንቶች በውይይታቸው ማጠቃለያ ላይ መግለጻቸው ታውቋል።
በቀናው ግጭትና ሁከት ከሚፍጥሩ የውጪ ጣልቃ ገብነቶች ራሱን ማላቀቅ እንዳለበት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ማሳሰባቸውን የሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል።
የሶማሊያው ፕሬዝደንት በበኩላቸው ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ በበኩላቸው ኤርትራ የሃገራቸውን ብሔራው ሠራዊት ለማተናከር ለምታደርገውን አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
የፕሬዝደንት ሃሳን ጉብኝት የመጣው ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከሁለት ሳምንታት በፊት አንካራ ላይ ሥምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።
ሁለቱ ሀገራት አንዱ የሌላውን ሉአላዊነት፣ እንዲሁም የግዛት አንድነት እንደሚያከብር በፈጸሙት ሥምምነት አስታውቀዋል። ሁለቱ ወገኖች በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለንግድ ጠቀሜታ የባሕር አቅርቦት እንዲኖራት ውይይት እንደሚያደርጉ ተስማምተዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝደንት ከሁለት ዓመታት በፊት ከተመረጡ ወዲህ አሥመራን ሲጎበኙ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።
ኤርትራ በርካታ የሶማሊያ ጦር ዓባላትን በማሠልጠን ላይ ስትሆን፣ የተወሰኑት ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ሃገራቸው በመመለስ በአል ሻባብ ላይ በሚወሰደው እርምጃ በመሳተፍ ላይ ናቸው።
መድረክ / ፎረም