በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያው ፕሬዝደንት አሥመራ ገቡ


የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ በኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ሲደረግላቸው፤ አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ኤርትራ፤ እአአ 25/2024
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ በኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ሲደረግላቸው፤ አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ኤርትራ፤ እአአ 25/2024

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል አንካራ ላይ ሥምምነት ከተፈፀመ ወዲህ የሶማሊያው ፕሬዝደንት በቀጠናው ጉብኝት ሲያደርጉ የመጀመሪያው ነው።

ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ አሥመራ ሲደርሱ በኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚያሳድጉበትና በዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ የኤርትራው የማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በX ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

የፕሬዝደንት ሃሳን ጉብኝት የመጣው ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከሁለት ሳምንታት በፊት አንካራ ላይ ሥምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።

ሁለቱ ሀገራት አንዱ የሌላውን ሉአላዊነት፣ እንዲሁም የግዛት አንድነት እንደሚያከብር በፈጸሙት ሥምምነት አስታውቀዋል። ሁለቱ ወገኖች በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለንግድ ጠቀሜታ የባሕር አቅርቦት እንዲኖራት ውይይት እንደሚያደርጉ ተስማምተዋል።

አሥመራ ባለፈው ጥቅምት የግብጽ እና የሶማሊያን መሪዎች ለሦስትዮሽ ውይይት ጋብዛ አስተናግዳለች። በውይይቱ የሦስቱ ሃገራት መሪዎች የሶማሊያን ተቋማት ለማጠናከርና ከውስጥና ከውጪ የገጠሟትን ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ ተስማምተዋል። በተጨማሪም የሶማሊያ ፌዴራል ሠራዊት ሽብርን እንዲጋፈጥና የሃገሪቱን ሉአላዊ ግዛት እንዲከላከል ለማስቻል ተስማምተዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ከሁለት ዓመታት በፊት ከተመረጡ ወዲህ አሥመራን ሲጎበኙ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።

ኤርትራ በርካታ የሶማሊያ ጦር ዓባላትን በማሠልጠን ላይ ስትሆን፣ የተወሰኑት ሥልጠናቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል።

ሶማሊያ፣ ግብጽ በአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ መወሰኗን በመልካም እንደምትቀበል አስታውቃለች፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG