የዩናይትድ ስቴትስ የአሁን እና የቀድሞ ፕሬዚደንቶች የደሕንነት ጥበቃ ተቋም የሆነው "ሴክሬት ሰርቪስ" ዋና ዲሬክተር ኪምበርሊ ቺትል ሥራቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ዲሬክተሯ ሥራቸውን የለቀቁት በቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ ተቋሙ ዋና ኃላፊነቱ የሆነውን የፕሬዚደንታዊ ጥበቃ እንዴት መወጣት ሳይችል ቀረ የሚለው ቁጣ እየተቀጣጠለ መምጣቱን ተከትሎ ነው።
በተቋሙ ዲሬክተርነት እአአ ከ2022 ነሀሴ ወር ጀምረው የሰሩት ኪምበርሊ ቺትል ዛሬ ለተቋሙ ሠራተኞች በላኩት የኢሜል መልዕክት ሥራቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ በፔንሲልቬንያ የምርጫ ዘመቻ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ ተተኩሶባቸው የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ የፕሬዚደንታዊ ደህንነት ኃላፊዋ "ሥራቸውን ይልቀቁ" የሚለው ጥያቄ የበረታ ሲሆን አጥቂው በዚያ ቅርበት የሪፐብሊካን ፓርቲው እጩ ፕሬዚደንት አጠገብ እንዴት ሊደርስ ቻለ በሚል በርካታ ምርመራዎች ተከፍተዋል።
ትላንት ሰኞ ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ተወካዮች ፊት ቀርበው ቃላቸውን የሰጡት ቺትል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንቶችን ደሕንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም "ሴክሬት ሰርቪስ" የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው በቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ ደሕንነት ጥበቃው በበርካታ አሰርት ዓመታት ባልታየ ደረጃ " እጅግ ከፍተኛ የአፈጻጸም ውድቀት" እንደነበረበት አምነዋል።
ትረምፕ ፔንሲልቬኒያ በትለር ከተማ ውስጥ በደጋፊዎች ስብሰባ ላይ ሳሉ የሃያ ዓመቱ ቶማስ ማቲው ክሩክስ አጠገቡ ካለ ህንጻ ጣሪያ ላይ ሆኖ ተኩስ በመክፈት እሳቸውን እና ሌሎች ሁለት ታዳሚዎችን ያቆሰለ ሲሆን አንድ ሌላ ሰው ገድሏል።
ከግድያ ሙከራው ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ትላንት ሰኞ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት ፊት ቀርበው ቃላቸውን የሰጡት የተቋሙ ዲሬክተር ኪምበርሊ ቺትል "አጥፍተናል በተቋማችን ለተፈጸመ ለማናቸውም የደሕንነት ጥበቃ ጥፋት ሙሉ ኃላፊነት እወስዳለሁ" ያሉት ዲሬክተሯ "በዚያ ዕለት የደረሰው ሁለተኛ እንዳይደገም በከፍተኛ ትጋት እሰራለሁ" ብለው ነበር።
ተቋሙ ስለተፈጸሙት ስህተቶች እያካሄደ ያለው ምርመራ ሃምሳ ቀናት ያህል እንደሚወስድ ተናግረው ምርመራው ሳይጠናቀቅ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት
ፈቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩት ዲሬክተሯ ሆኖም ስራቸውን እንደማይለቁ መናገራቸው የምክር ቤቱ የቁጥጥር ኮሚቴ ሪፐብሊካን እና ዲሞክራት አባላትን አስቆጥተው ነበር።
የምክር ቤቱ የደሕንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባል ማይክ ተርነር "ለሥራው ብቁ አለመሆንዎን አሳይተዋል። መልቀቅ አለብዎ በፈቃድዎ የማይለቅቁ ከሆነ ፕሬዚደንት ባይደን ሊያባርሩዎ ይገባል’ ብለዋቸዋል።
መድረክ / ፎረም