በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በሼኩ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሀገር የንግድ ተቋማትን ሥራ አያስተጓጉልም” – የሼክ መሐመድ ቃል አቀባይ


ሼክ ሞሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ
ሼክ ሞሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ

የሳውዲ አረቢያ መንግስሥት በሙስና ከጠረጠራቸውና በቁም እስር ከሚገኙት የመንግሥት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች መካከል የሚገኙት ኢትዮጵያዊ ትውልድ ያላቸው የሳውዲ ቱጃር ሼክ ሞሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በሳውዲ መንግሥት እየተመረመሩ መሆኑንና የታገደው ንብረታቸው ከሳውዲ ውጪ ያለን አያካትትም ሲሉ ለንደን የሚገኙት የሼኩ ቃል አቀባይ ለአሜሪካ ድምፅ ገለፁ።

በለንደን የሚገኙት የሼህ መሐመድ ቃል አቀባይ ቲም ፔን ድሬይ ስለሁኔታው ከአሜሪካ ድምጽ ተጠይቀው በኢሜል በሰጡን ምላሽ ፤ ሼኩ በሪያድ ሪትዝ-ካርልተን ሆቴል በቁጥጥር ስር እንደሚገኙ አረጋግጠውልናል። በዚሁ ምላሽም፤ ".. በሳውዲ አረቢያ የተያዙ የተለያዩ አይነት ምርመራዎችና ጥያቄዎችን ሼኩ በጽኑ ያስተባብላሉ። የንጉሳዊ ግዛቷ የሀገር ውስጥ ጉዳይ በመሆኑ በዝርዝር የምንሰጠው አስተያየት ባይኖርም፤ ሁኔታው በሼኩ የሚንቀሳቀሱ የውጭ-ሀገር የንግድ ተቋማትን ስራ እንደማያስተጓጉል ለመግለጽ እንወዳለን።" ብለዋል።

“በሼኩ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሀገር የንግድ ተቋማትን ሥራ አያስተጓጉልም” – የሼክ መሐመድ ቃል አቀባይ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:46 0:00


የቀደመ ዘገባ

በሳውዲ አረቢያ መንግስሥት በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ልዑላን፣ ሚኒስትሮች የቀድሞ ሚኒስትሮችና ባለሃብቶች የአብዛኞቹ የባንክ ሂሳብ መታገዱን የሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮች አረጋገጡ።

ከታሳሪዎች መካከል ኢትዮጵያዊ ትውልድ ያላቸው የሳውዲ ቱጃር ሼክ ሞሐመድ አል-አሙዲ የሚገኙበት ሲኾን እስረኞቹ ታስረውበታል ከተባለው ሪትስ ካርልተን ሆቴል ወጥቷል የተባለውና ሮይተርስ የላከልን አጭር የቪዲዮ ምስል የሚያሳየው ፤ "በሆቴሉ የእንግዳ መቀበያ ውስጥ በተነጠፈ ፍራሽ ላይ ብርድ ልብስ የለበሱ ሰዎች ተኝተውና አጠገባቸውም መሳሪያ ተቀምጦ ነው።"

ሼክ ሞሐመድ አል-አሙዲን በተመለከተ በኢትዮጵያ ካሉ የሥራ አጋሮቻቸውና ወዳጆቻቸው መረጃ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም በሮች በሙሉ ዝግ ሆነውብናል።

የሳውዲ አረቢያ መንግስሥት በሙስና ከጠረጠራቸውና በቁም እስር ከሚገኙት የመንግሥት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች መካከል ኢትዮጵያዊ ትውልድ ያላቸው የሳውዲ ቱጃር ሼክ ሞሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ይገኙበታል።

ቅዳሜ ዕለት ከታሰሩት የንጉሳዊ ቤተሰብ አባላትና ሚኒስትሮች መካከል ቢሊየነሩ ዋሊድ ቢል ታል፤ የቀድሞ የብሔራዊ ክቡር ዘበኛ ጦር ኃላፊ፤ የቀድሞ የገንዘብ ሚንስትርና ሌሎችም ባለሥልጣናትና ባለሃብቶች እንደሚገኙበት ታውቋል።

የሳውዲ አረቢያ አልጋወራሽ ሞሀመን ቢን ሳልማን በጀመሩት የጸረ ሙስና ዘመቻ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ዐስራ አንድ ልዑሎች፣ አራት ሚኒስትሮችና ከዐስር በላይ የቀድሞ ሚኒስትሮች የሚገኙበት ሲኾን፤ ሼክ ሞሐመድ አሊ አል-አሙዲም በሪትስ ካርልተን ሆቴል የቁም እስር ላይ ከዋሉት ስም ዝርዝር ውስጥ ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙት የሼክ ሞሐመድ አል-አሙዲ ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው እስከ ትላንት እሁድ ጠዋት በስልክ አግኝተዋቸው እንደነበር ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“በእኔ በኩል እንደማንኛውም ሰም ከምሰማው በስተቀር የደረሰኝ መረጃ የለም። ከእርሳቸው ጋር እስከ ትላንት ድረስ በስልክ እየተገናኘን ነበር ምንም የማውቀው ነገር የለም። ለሥራ ጉዳይ እርሳቸው ሲደውሉልኝ ካልሆነ በስተቀር እኔ ወደ እርሳቸው የምደውልበት መንገድ የለም” ብለዋል።

የአሜሪካ ድምፅ ምንጮች እንዳረጋገጡት ሼክ መሐመድ ከትናንት ጠዋት በኋላ የስልክ ግንኙነታቸው ተቋርጧል። በአሁኑ ሰዓትም የተፈቀደላቸው ከአንድ ሰው ጋር ብቻ እንዲገናኙን ነው። ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ በአብዛኞቹ የሚድሮክ አመራር አባላት ዘንድ መደናገጥ መፈጠሩን የጠቆሙን ምንጮች ከተባራሪ መረጃ ውጪ ቀጣዩ ሁኔታቸውን በተመለከተ ምንም መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቁመውናል።

የሼክ መሐመድን ሁኔታ በቅርብ ያውቃሉ ተብሎ የሚገመተው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋ ይርዳው ልናገኛቸው ሞክረን ከሀገር ውጪ መሆናቸው ተገልፆልናል።

የደርባ ሚድሮክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ አሰግዴን ስለሁኔታው ጠይቀናቸው ነበር “እኔም የማውቀው እናንተ የምታውቁትን ያክል ነው” ብለውናል። አያይዘውም “ልክ እናንተ የሰማችሁትን እኛም ሰምተናል ለማጣራት እያሰብን ነው። እርሳቸው በሰላም እንዳሉ ግን እናውቃለን ብለዋል።

15.3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የተመዘገበ የሀብት መጠን ያላቸው ሼክ መሐመድ ዋነኛ የሐብት ምንጭ የነዳጅ ዘይት እንደሆነ ይነገራል። በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ማዕድን፣ ኮንስትራክሽን፣ ሪልስቴት፣ የማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችና በፋይናንስና ሥራ ላይ ተሰማርተው ከ70 ኩባንያዎችና ከ40 ሺሕ በላይ ሠራተኛ ያላቸው ባለሃብት ናቸው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ ለልማት የወሰዷቸውን ቦታዎች ለረጅም ዓመታት አጥረው በማስቀመጥ ስማቸው የሚነሳ ባለሃብት ናቸው። ከድርጅቶቻቸው መካከል ታክስ ባለመክፈል ክስ ተመስርቶባቸውም ያውቃል።

የሳውዲ አረቢያ አልጋወራሽ ሞሃመን ቢን ይህንን የማሰር እርምጃ የወሰዱት አዲስ በመካሄድ ላይ ካለው ፀረ ሙስና ምርመራ ሕግ ጋር በተያያዘ ሲሆን በዚህም የተያዙት ሰዎች አብዛኞቹ ከሳውዲ መንግሥት ፕሮጀክቶችን ወስደው ባለመሥራት ወይም ባለመጨረሳቸው እንደሆነ እየተነገረ ነው። በዚም ምክኒያት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ ተመዝብሯል ተብሏል።

አንዳንድ ተንታኞች የሳውዲውን ንጉስ እርምጃ፤ ወደፊት ሀገራቸውን ለመለወጥ የያዙትን አጀንዳ እንዳያስፈጽሙ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ገለል ያደረጉበት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የመካከለኛው ምስራቅ ኢንስቲቱት ተመራማሪ ዙቤር ኢቅባል ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ሲናገሩ፥ የአልጋ ወራሹ አርምጃ በሳውዲ ውስጥ ለውጥ በሚሹ ወጣቶችና በቆየው ትውልድ መካከል በሳውዲ ልዑላዊ ቤተሰብ ውስጥ መኖራቸውን አስረድተዋል።

የሳውዲ አረቢያ መንግስት በ500 ቢልዮን ዶላርስ ወጭ የኢንዱስትሪና የፈጠራ ስራ ማእከል ለመገንባት ያለውን እቅድ ባለፈው ወር ያስታወቀ ሲሆን፤ የሀገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ የለዘቡ የሃይማኖት መርሆዎች የሚታዩባት ለለውጥ የተዘጋጀች እንድትሆን ታስቧል።

የሳውዲ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት 11 ልዑላንና 38 ታዋቂ ባለሀብቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ታውቋል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG