በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ባለታሪክ ፖል ሩሲሳቢጊና ተፈረደባቸው


የሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ባለታሪክ ፖል ሩሲሳቢጊና
የሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ባለታሪክ ፖል ሩሲሳቢጊና

በሆቴል ሩዋንዳ ፊልም የጀግንነት ታሪካቸው የተወሳላቸው ፓል ሩሴሳባጊና በተመሰረተባቸው የሽብር አድራጎት ክስ ሃያ አምስት ዓመት እስራት ቅጣት እንደተፈረደባቸው ተገለፀ። ደጋፊዎቻቸው የፍርድ ሂደቱን ሃሰተኛ ሲሉ ኮንነውታል።

የስድሳ ሰባት ዓመቱ ሩሴሳባጊና የተመሰረቱባቸውን ክሶች ያስተባበሉ ሲሆን አሁን በተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ይግባኝ ለማቅረብ የአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

የቀድሞው የሆቴል ሥራ አስኪያጅ የበኋላው የትግል መሪ ላይ የሩዋንዳው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈው ዛሬ ሰኞ ሲሆን ደጋፊዎቻቸው ሂደቱ ፍትህ የጎደለው አስቀድሞ የተቀነባበረ ውሳኔ ሲሉ ተችተዋል።

እርሳቸው እና ሊሎች ሃያ ሰዎች የተከሰሱት የሩዋንዳ መንግሥት የሽብር ጥቃት በመፈጸም ከሚወነጅለው ብሄራዊ ነጻ አውጭ ኃይሎች ከተባለው ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ነው።

ዳኛው ውሳኔውን ለችሎቱ ሲያሰሙ

"ሩሴሳባጊና የሽብርተኛ ድርጅት በማቋቋም እና አባል በመሆን ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል" ብለዋቸዋል።

የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ ዮላንዴ ማኮሎ ተከሳሾቹ ሊከላከሉት የማይችሉት ማስረጃ ቀርቦባቸዋል ብለዋል። ቀደም ሲል አንድ የሩዋንዳ መንግሥት ጋዜጣ ባወጣው ሪፖርት አቃቤ ህግ የታውቁ የፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የመንግሥታቸው ነቃፊ የሆኑት ፓል ሩሴሲባጊና ዕድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድባቸው ጠይቋል ብሎ ነበር።

የፖል ሩሴሲባጊና ቤተሰቦች እና ደጋፊዎች እአአ በ1996 ሃገራቸውን ጥለው ከወጡ በኋላ የቤልጂየም ዜግነት የወሰዱት እና የዩናትድ ስቴትስ ነዋሪም የሆኑት ፖል ሩሴሲባጊናን ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር አታልለው ወደሩዋንዳ ወስደዋቸዋል ብለዋል።

ወደዱባይ ከተጓዙ በኋላ በግል አውሮፕላን ኪጋሊ ተወስደው እንደታሰሩ ነው የተገለጸው። ከታሰሩ በኋላ በሰጡት ቃል ቡሩንዲ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን ንግግር ለማድረግ አንድ ጓደኛዬ ጋብዞኝ ስለነበር ወደዚያ ለመጓዝ ያሳፈሩኝ መስሎኝ ነበር ብለዋል።

ከጠበቆቻቸው አንዷ ኬት ጊብሰን ለቪኦኤ በሰጡት ቃል "ፖል በትክክል ለመዳኘት ዕድል አልተሰጣቸውም፥ የተወሰነባቸው ቅጣት ከመጠለፋቸው አስቀድሞ የተዘጋጀ ነው" ብለዋል።

ጉዳዩን የሚከታተሉ ነጻ ወገኖችም በጠበቃዋ አስተያየት ይስማማሉ። የአሜሪካ ጠበቆች ማኅበር፥ የሰብዓዊ መብቶች ማእከል እና የክሉኒ የፍትህ ተከታታይ ፋውንዴሽን የጠበቃዋን አስተያየት አስተጋብተዋል።

XS
SM
MD
LG