ዋሺንግተን ዲሲ —
የሩዋንዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት "ሆቴል ሩዋንዳ" በተባለው ዝነኛ ፊልም በጀግንነት በተተረከላቸው ታሪካቸው የሚታወቁትን ፖል ሩሲሳቢጊና እና ሌሎችም ተከሳሾች በተመሰረተባቸው ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ ክሶች የጥፋተኛነት ውሳኔ ሰጠ።
የፖል ሩሲሳቢጊና ጠበቆች እና ቤትሰቦች ይህ ውሳኔ ባለፈው ዓመት ከመታገታቸው በፊት የተዘጋጀ መሆኑ የታወቀ ነው ብለዋል።
በአንድ የሩዋንዳ መንግሥት ጋዜጣ በወጣ ዘገባ መሰረት አቃቤ ህግ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድባቸው ጠይቁዋል።
ከጠበቆቻቸው አንዷ ኬት ጊብሰን ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ፖል በትክክል ለመዳኘት ዕድል አልተሰጣቸውም፣ የተሰጣቸው ከመጠለፋቸው አስቀድሞ የተሰናዳ ፍርድ ነው ብለዋል።
ጉዳዩን የሚከታተሉ ነጻ ወገኖችም በጥበቃዋ አስተያየት ይስማማሉ፣ የአሜሪካ ጠበቆች ማኅበር የሰባአዊ መብቶች ማእከል እና የክሉኒ የፍትህ ተከታታይ ፋውኒዴሺን የጠበቃዋን አስተያየት አስተጋብተዋል።