በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ እስራኤልን ወቅሳ ሦሪያ በአስቸኳይ እንድትረጋጋ ጥሪ አቀረበች


ፎቶ ፋይል፦ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ
ፎቶ ፋይል፦ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ

ክሬምሊን ሦሪያ በአስቸኳይ ተረጋግታ ማየት የምትፈልግ መሆኗን አስታውቃለች፡፡ የእስራኤልን የአየር ጥቃት ማድረሷን እና በጎላን ኮረብቶች “ከጦር ነጻ ቀጠና” መመሥረቷን ተችታለች፡፡ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የሀገሪቱ ሁኔታ በተቻለው መጠን በአስቸኳይ ተረጋግቶ ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡

ፔሽኮቭ አክለውም “የአየር ጥቃቶቹ፣ በጎላን ኮረብቶች የተፈጸሙ ድርጊቶች እና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ቀጠና መከለሉ ቀድሞውንም ባልተረጋጋችው ሦሪያ ሁኔታውን ለማረጋጋት ብዙም አስተዋፅዖ አይኖረውም።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሞስኮ የረጅም ጊዜ አጋሯን ባሻር አል አሳድን ከአማጽያኑ ቅጽበታዊ ጥቃት ለመከላከል ያልቻለችው በዩክሬን ወደ ሦስት ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ በምታካሂደው ጥቃት ምክኒያት ሊሆን እንደሚችል የተነሳ ሲሆን አሁንም “የዩክሬይኑ ጦርነት ግንባር ቀደም ትኩረቷ” ሆኖ እንደሚቀጥል አመልክታለች፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ከአዲሱ የሦሪያ አመራር ጋር በሀገሪቱ ስላለው የሩሲያ ወታደራዊ መሠረተ ልማት የወደፊት ዕጣ መነጋገሯን እንደቀጠለች ተናግረዋል፡፡

"በሦሪያ ያለውን ሁኔታ ከሚቆጣጠሩት ጋር ግንኙነት አለን፡፡ የጦር ሠፈሮቻችን እና ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኳችን እዚያ ስላሉ ይህ መሆኑ አስፈላጊ ነው" ብለዋል ፔስኮቭ፡፡

በሦሪያ የሚገኙት ታርቱስ የባሕር ኅይል የጦር ሠፈር እና ሃሜሚም አውሮፕላን ማረፊያ ሩሲያ ከሀገር ውጪ ያሏት ብቸኞቹ የጦር ሠፈሮቿ ሲሆኑ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአፍሪካ በምታካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ናቸው።

እአአ የ2015ቱ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት የሦሪያን የእርስ በእርስ ጦርነት አቅጣጫ ቀይሮታል፡፡ ቁጥር ሥፍር ከሌላቸው አማፂ ኅይሎች ጋር ሲዋጋ የኖረውን የአሳድ መንግሥት ሩሲያ የታደገቸው መሆኑም በስፋት ይነገራል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG