በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሳይንቲስቱ ዶ/ር ተወልደብርሀን ቀብር ተፈፀመ


የሳይንቲስቱ ዶ/ር ተወልደብርሀን ቀብር ተፈፀመ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:08 0:00

የሳይንቲስቱ ዶ/ር ተወልደብርሀን ቀብር ተፈፀመ

በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የብዝሀ ህይወት ሳይንቲስት እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቹ ዶ/ር ተወልደብርሀን ገ/እግዚአብሔር፣ የቀብር ሥነስርዓታቸው ዛሬ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በተገኙበት የቀብር ሥነ ስርዓት የሎሬት ዶ/ር ተወልደብርሀን የህይወት ታሪክ ተነቧል። ሳይንቲስቱ በብዝሃ ህይወት እና በአካባቢ ጥበቃ ዙርያ ላደረጓቸው ምርምሮች ሌሎች አስተዋፆች በርካታ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ሽልማቶች አግኝተዋል፡፡

የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም በትግራይ ክልል ዓድዋ አካባቢ በምትገኝ ርባገረድ በምትባል መንደር ውስጥ የተወለዱት ዶ/ር ተወልደብርሀን ገብረእግዚያብሔር ፣ በ 83 ዓመታቸው በተወለዱበት ቀን በትናንትናው ዕለት መጋቢት 12 ቀን ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡ በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት ስርዓተ ቀብራቸው በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡

በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ የተነበበው የሎሬት ዶ/ር ተወልደ ብርሀን የሕይወት ታሪክ፣ በ1958 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣ በ1958 ዓ.ም በከፍተኛ ነጥብ በመጀመሪያ ዲግሪ ሲመረቁ ከአፄ ኃይለስላሴ እጅ የወርቅ ሽልማት መቀበላቸውን ያመለክታል።

በ1960 ዓ.ም በእንግሊዝ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምሕርነትና የሳይንስ ፋካልቲ ዲን በመሆን ማገልገላቸው ተጠቅሷል፡፡ ከ978 እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ደግሞ አስመራ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡

በ1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ግቢ የሚገኘው የዕፅዋት ጀኔቲክስ ባንክ ሲመሰረት የካውንስል አባል ሆነው ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዕፅዋት ስያሜ እና ስርጭትን በሚመለከት በርካታ ምሑራንን አሰልጥነዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ የዕፅዋት ቤተ መዘክርን በመገንባት ተማሪዎቻቸው እንዲማሩበት እና እንዲመራመሩበት አድርገዋል፡፡ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የሳይንሰስ ቃላትን ወደ አማርኛ በመተርጎም ተገቢ ፍቺን በማስቀመጥ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

የምርምር ሥራዎቻቸውን በበርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ጆርናሎችና በመፅሐፍት አሳትመዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በብዝሀ ህይወት ሀብት እና ደህንነት ዙርያ ተሟግተዋል፡፡ የማኅበረሰብ የፈጠራ መብት ባለቤትነት እንዲከበርም 77 የዓለማችን ታዳጊ ሀገራትን ወክለው በዓለም መድረክ ተከራክረዋል፡፡

ለነዚህ እና ለሌሎች አስተዋፅኦዎቻቸው በ1993 ዓ.ም የአማራጭ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በ1998 ደግሞ እንዲሁ የምድራችን ጀግና የተሰኘውን ሽልማት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብር አሸንፈዋል፡፡

ዘ ጋርዲያን የተባለው የውጭ ሀገር ጋዜጣ እአአ በ2008 ዓ.ም ከዓለማችን 50 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ዶ/ር ተወልደን አንዱ አድርጎ መርጧቸዋል፡፡ እንደዚሁም ሌሎች የውጭ እና የሀገር ውስጥ ሽልማቶችን ማግኘታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያሳያል፡፡

ዶ/ር ተወልደብርሀን በብዝሀ ህይወት እና በአካቢ ጥበቃ ዘርፍ ከመመራመር አልፈው የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው መርተዋል፡፡ ለዘርፉ አስፈላጊ የሆኑ ፖሊሲዎች እንዲወጡም አስተዋፆ አድርገዋል፡፡

ዶ/ር ተወልደብርሀን በትውልድ እንግሊዛዊት፣ በዜግነት ደግሞ ኢትዮጵያዊት ከሆኑት ባቤታቸው ሱ ኤድዋርድ ሦስት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ከ60 በላይ የሚሆኑ ልጆችን ደግሞ አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG