በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የብዝሀ ሕይወት ሳይንቲስቱ ዶ/ር ተወልደብርሀን አረፉ


የብዝሀ ሕይወት ሳይንቲስቱ ዶ/ር ተወልደብርሀን አረፉ
የብዝሀ ሕይወት ሳይንቲስቱ ዶ/ር ተወልደብርሀን አረፉ

በብዝሀ ሕይወት እና በአካባቢ ጥበቃ ዙርያ ብዙ ምርምሮችን የሠሩትና በሥራቸውም ብዙ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኙት ዶ/ር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

በዶ/ር ተወልደብርሃን ሕይወት ማለፍ ሐዘኑን የገለፀው የግለታሪካቸው ጸሐፊ ዘነበ ወላ፤ “በሀገሩ፣ በወገኑ እና በራሱ ማኅበረሰብ ጥሩ አስተዋፅኦ ካደረጉ እና ተጠቃሽ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው፡፡ ዓለም ለወደፊት ስለ አካባቢ ጥበቃ አሳቢዎቿ በምትፅፍበት ጊዜ ከአውራዎቹ አንዱ ዶ/ር ተወልደ ይሆናል፡፡” ብሏል።

ዘነበ ወላ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጠው አስተያየት “ዶ/ር ተወልደ አንተን የሚተካ ሰው ፈጥረሃል ወይ ብዬ ስጠይቀው፣ እኔ መተካት አለብኝ ብዬ የማስብ ሰው አይደለሁም፣ ማስተማር እኮ ራስህን መተካት ነው” ብሎኛል፡፡ የዶ/ር ተወልደብርሀን ሕርሳብ ተሰሚነት አግኝቶ ቢተገበር ኖሮ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ለማዳበሪያ ግዢ በቢሊዮን የሚገመት ወጪ አታወጣም ነበር፡፡” ብሎናል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እና የዶ/ር ተወልደብርሀን ተማሪ እና የቅርብ ሰው የነበሩት ፕሮፌሰር እንደሻው በቀለ ለቪኦኤ በሰጡት አስተያየት ፤ “ተወልደ ለኢትዮጵያ ባለውለታዋ ነው፡፡

ለአፍሪካም ባለውለታዋ ነው፣ ኢትዮጵያ በብዝሀ ሕይወት ብዝበዛ እንዳትጎዳና ጥቅም አልባ እንዳትሆን ብቻውን የተከራከረና ተከራክሮም ያሸነፈ ሰው ነው፡፡ አማራጭ የኖቤል ሽልማት ያሸነፈውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡” ብለዋል።

በትግራይ ክልል፣ ዓድዋ አካባቢ በምትገኝ ርባገረድ በምትባል መንደር በ1932 ዓ.ም የተወለዱት ዶ/ር ተወልደብርሀን ገ/እግዚአብሔር የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርታቸውን በዓድዋ ከተማ ንግስተ ሳባ ት/ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡

በ1959 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁት ዶ/ር ተወልደብርሀን በመቀጠልም በእንግሊዝ ከሚገኘው ኖርዝ ዋለስ ዩቪቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ዶ/ር ተወልደብርሀን በሕይወት ዘመናቸው በብዝሀ ሕይወት እና በአካባቢ ጥበቃ ዙርያ ብዙ ምርምሮችን ሠርተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ግንባር ቀደም የአካባቢ ጥበቃ እና የአርሶ አደሮች መብት ተሟጋች ነበሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በአስመራ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በመሪነት ያገለገሉት ዶ/ር ተወልደብርሀን፣ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነውም ሠርተዋል፡፡

በምርምር ሥራዎቻቸው እና በአካባቢ ጥበቃ አመራራቸው ላስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም የተሰጣቸው የአማራጭ የኖቤል ሽልማት እና በ 2006 ዓ.ም ያሸነፉት ቻምፕዮን ኦፍ ዘ ኤርዝ (የምድራችን ጀግና) የተሰኘው ሽልማት ተጠቃሽ ናቸው።

XS
SM
MD
LG