የኢትዮጵያውያን የሽልማት ድርጅት በሰሜን አሜሪካ፤ በእንግሊዝኛ ምሕጻረ ቃሉ - SEED (ማኅበረ ግዩራን ዘረ-ኢትዮጵያ) በሃያ አምስተኛ ዓመት የኢዮ-በልዩ ክብረ-በዓሉ ከሥነ ጥበቡ ዘርፍ፥ ቴዲ አፍሮን፥ ለምን ሲሳይን፥ እና አንጋፋውን ድምጻዊ መሃሙድ አህሙድን፤ በበጉ አድራጎት ሥራቸው የገዳሙን አገልጋይ አባ ከፍ ያለው አበራን፤ በዩናይትድ ስቴትስ ለድሆች ነጻ ሕክምና በመስጠትና በሌሎች መልካም ምግባሮቻቸው የሚታወቁትን ዶ/ር አምባቸው ወረታን፤ “ሃኪሞች ለአፍሪቃ” የተባለውን የበጎ አድራጎት ተቋም መሥራች አቶ ቴድ ዓለማየሁንና የሕክምና ምርምር ባለ ሞያውን ዶ/ር ዛኪ ሸሪፍን ጨምሮ “ለሕብረተሰብ ጥቅም የሠሩ፤ የማሕበረሰብ ጉዳይ ግድ የሚላቸው” ያላቸውን ሰባት ኢትዮጵያውያን ያከብራል።
ማኅበረ ግዩራን ዘረ-ኢትዮጵያ በተጨማሪም ለኢትዮጵያውያን ሴቶች መብት በመታገል ይታወቁ የነበሩትንና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ዶ/ር ማይገነት ሽፈራውንም በክብር ያስታውሳል። ሁለት የድርጅቱ ቦርድ አባላት ሌሎች ተያያዥ ቁም ነገሮችም በራዲዮ መጽሔት ያጫውቱናል።
ቴዲ አፍሮ ቀጠሮ ለተያዘለት ቃለ ምልልስ በራዲዮ መጽሔት የ‘ጥበብ እና የጥበበኛው መስኮት’ ብቅ ብሎ ከአሜሪካ ድምጽ ስቱዲዮ እንገናኝ ይላል።
ውበት በሴት ገጣምያን ዓይን ወይም ብዕር “የተሻለ ይሳላል” ትለናለች፤ ወጣቷ ገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ።
“መልስ አልባ ጥያቄ”..“ፍቅርና ጃዝ” .. “እረ-አምሳለ” እና ሌሎችም.. ሥነ-ግጥም ለዛና ቁም ነገር ከተታታይ ቃለ ምልልሱ ያገኛሉ።
ንጉሴ አክሊሉ በአዲስ አበባ የድምጽ መስኮቱ “አሜሪካ ትቅደም” በሚለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ መርህ ቃል .. “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለው ሃረግ እና እሳቤ ከአርባ ሦሥት ዓመታት በኋላ ታወሰኝ” ይለናል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ