በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ተመድ በኮሮናቫይረስ ጉዳይ ቻይናን በተጠያቂነት እንዲይዛት ትረምፕ አሳሰቡ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኮሮናቫይረስ ጉዳይ ቻይናን በተጠያቂነት እንዲይዛት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አሳሰቡ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሳሰቡት ለመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አስቀድሞ ተቀርጾ ዛሬ በተላለፈው ንግግራቸው ላይ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ከዋይት ኃውስ ባስተላለፉት ንግግራቸው በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ሠላሳ አንድ ሚሊዮን ሰዎች የተያዙበት እና ከዘጠኝ መቶ ስድሳ ሽህ የሚበልጡ ለህልፈት ለዳረገው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መዛመት ቻይና ተጠያቂ ነች ብለዋል።

ቫይረሱ በተቀሰቀሰበት ጊዜ ቻይና የሃገር ውስጥ ጉዞዎችን ሰርዛ በረራዎች ከሀገር ውጭ እንዲወጡ በመፍቀድ ቫይረሱን አዛምታለች ብለዋል።

አስከትለውም የቻይና መንግሥትና ቻይና በግልጽ የምትቆጣጠረው የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ ከሰው ወደሰው እንደሚተላልፍ ማሰረጃ የለም ብለው በሀሰት አወጁ ሲሉ ፕሬዚዳንት ትረምፕ ወንጅለዋል።

በሆፍስትራ ዩኒቨርስቲ የህግ ፕሮፌሰር ጁሊያን ኩ ሲናገሩ ፕሬዚዳንት ትረምፕ በዚህ ንግግር ቻይና ላይ ያሰሙት ውንጀላ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የጠቅላላ ጉባዔ ንግግር ባልተለመደ ደረጃ ጠንካራ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።

ትረምፕ ቻይናን ለቫይረሱ መዛመት ተጠያቂ ማድረጋቸውና የቻይና ቫይረስ ሲሉ መጥራታቸው ቻይናን በኃላፊነት እንድትጠየቅ ዓለምቀፍ ድጋፍ ለማግኘት እንደፈለጉ አመልካች ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር ኩ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ሲያብራሩ የፕሬዚደት ትረምፕ ንግግር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እርምጃ እንዲወሰድባት የሚያሳምን ምሁራን እንደሚጠራጠሩ ገልጸዋል።

ሆኖም ቻይና ዓለምቀፉ ወረርሽኝ ከምን እንደተቀሰቀሰ እና ስለተዛመተበት አኳሃን በሚካሄዱ ዓለምቀፍ ምርመራዎች ሙሉ በሙሉ እንድትተባበር ጫናውን ሊያበረታባት ይችል ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።

የቻይና ፕሬዚደንት ሺ ዢንፒንግ ባስተላለፉት አስቀድሞ የተቀዳ ንግግራቸው ዓለምቀፉን ወርርሽኝ የፖሊቲካዊ ለማደርግ ሚፈጸም ማናቸውም ሙከራ ተቀባይንት ሊኖረው አይገባም ብለዋል። ለወርርሽኙ የሚሰጠውን ዓለምቀፋዊ ምላሽ መሪነት ለዓለም የጤና ድርጅት መሰጠት አለበት ሲሉም የቻይናው መሪ አሳስበዋል

በዓለምቀፉ ወረርሽኝ ከዩናይትድ ስቴትስ ይበልጥ የተጠቃ ሃገር የለም። በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ መረጃ መሰረት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በበሽታው ሳቢያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ200ሺህ አልፏል። በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ከስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን አልፈዋል።

ፕሬዚዳንቱ በወረርሽኙ አያያዛቸው አንዳንድ የቀደሙ የእሳቸው አስተዳደር ባለሥልጣናት ጭምር ክፉኛ ይተቻሉ።

ፕሬዚዳንቱ በንግራቸው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባልታየ መልኩ ጠንካራ እንቅስቃሴ ያደረግንበት በማለት የወርርሽኙን ምላሻቸውን ተካላክለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ታከፋፍላለች ቫይረሱን ድል እናደርገዋለን ወረርሽኙ ይወገዳል ብለዋል።

XS
SM
MD
LG