የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ማይክ ፓምፔዬ፣ በትናንትናው እለት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣የአሜሪካ ድምጽ ቪኦኤን ዋና መ/ቤት ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸውም ወቅት፣ ስለ ዩናይትድ ስቴትሱ የዜና ማሰራጫ ተቋም አስፈላጊነትና፣ አሜሪካ በዓለም ላይ ስላለት ልዩ ጸጋ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ቆይታቸው በዲፕሎማሲ አገልግሎታቸው በተዘዋወሩባቸው አገሮች፣ የተናገሯቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችና ጭብጦችን በድጋሚ አንሰተዋቸዋል ፡፡
“በአገኘሁት አጋጣሚ ለሚያደምጡኝ ሁሉ፣ ስለ አሜሪካ ልዩ ጸጋ እነግራቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም እውነት ነው፡፡ አሜሪካ መልካምና ትልቅ ናት፡፡ መሰረታችንን ማወቅ የሚፈልግ ሁሉ ይህን መረዳት ይችላል፡፡ ሁል ጊዜም ህብረቷና አንድነቷ ፍጹም የጠነከረ አገር እንድትሆን እንጥራለን፡፡ ይህን ስናደርግ ሁል ጊዜም ላይሳካልን ይችል ይሆናል፡፡ ስለ ትናንቱም ሆነ ስለ ዛሬያችን ኩሩ እና ትሁትም ልንሆን ይገባናል፡፡”
ማይክ ፓምፔዮ የተናገሩት፣ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤትን ህንጻ፣ በአመጽ ከወረሩ ቀናት በኋላ ነበር፡፡
የአሜሪካ ዴሞክራሲ አምሳያ በሆነው ስፍራ የታየው ሁከት፣ የመላውን ዓለም ትኩረት ስቦ፣ አብይ ዜና ለመሆን በቅቷል፡፡
ፓምፔዮም ባለፈው ሳምንት ድርጊቱን ማውገዛቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ ከዚያ ወዲህ ግን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡበትም፡፡
ለአሜሪካ ድምጽ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ ባለሙያ፣ እሳቸው ከሚናገሩበት ህንጻ እልፍ ብሎ ባለ ህንጻ ላይ ስለተፈጸመው ጉዳይ፣ ፓምፔዮ አለማንሳታቸውም ሆነ ስለጉዳዩም አለመጠየቃቸው፣ ያስደነገጣቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከጀመርን ማርሻል ፈንድ ማይክ ኪማጅ እንዲህ ብለዋል
“ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፓፕሜዮ ባላፈው ሳምንት ስለተካሄደው አመጽ አለማንሳታቸው አስገራሚ ነበር፡፡ ይህ በእውነቱ በእያንዳንዱ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ያለ ነገር ነው፡፡ ያንን ሳይጠቅሱ ያለፉበትን ምክንያት መገመት የሚቻልበት ክፍተት ቢኖርም ፣ ጉዳዩን ሳያነሱ ማለፋቸው እንግዳ ነገር ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ለአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤን) እና ለሌሎች የዜና ማሰራጫዎችን በጀት በመመደብ፣ በመላው ዓለም ላሉ አድማጮች በርከት ባሉ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ዜና እና መረጃዎችን እንዲያደርሱ ያደርጋል፡፡
ፓምፔዮ፣ የአሜሪካ ድምጽ ቪኦኤ፣ ልዩ የሆነችው አሜሪካ ድምጽ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሚዲያ ስርጭት፣ የዩናይትድ ስቴትስን አስተሳሰቦች በመላው ዓለም የማስተዋውቅ ቁልፍ ሚና ያለው ሲሆን፣ አምባገነን መንግስታት መድረክ የሚያገኙበ ስፍራ ግን አይደለም ብለዋል፡፡ ስለዚሁም ሲናገሩ፤
“የቻይና ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ መንግሥታት ዓይነቶቹ አሜሪካ ለተመሰረተችበት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ክብር ደንታ የላቸውም፡፡ እነዚያ መንግሥታት አገራችን ለቆመችለት ነገር ሁሉ ጠላቶች ናቸው፡፡ መንግሥታት የሚኖሩት ህዝብን ለማገልገል መሆኑን እናውቃለን፡፡ እነሱ ግን ህዝብ የተፈጠረው መንግሥትን ለማገለግል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቪኦኤ ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ እናንተ የነጻነት ጦር ጫፍ ናችሁ፡፡” ብለዋል፡፡
ማይክ ፓምፔዮ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማት ቁንጮ ሆነው የሚያገለግሉበት የሥራ ዘመን ይህ ወር ሳይገባደድ ያበቃል፡፡ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቀደም ሲል በውጭ ጉዳይ ምኒስቴር ረዳት ጸሀፊ የነበሩትን አንተኒ ብሊንከንን አጭተዋል፡፡ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ካጸደቃቸው ብሊንከን ቀጣዩ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ይሆናሉ፡፡ (ዘገባው የቪኦኤ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዘጋቢ፣ ስንዲ ሴይን ነው፡፡)
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡