ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በዋስ እንዲፈቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ከእስር ቤት ሲወጡ በድጋሚ ተይዘው የነበሩት፣የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ድኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ዛሬ ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ ፣ ከእስር ተፈተው ከቤተሰቦቻቸው ጋራ መቀላቀላቸውን ባለቤታቸው ወይዘሮ ስንታየኹ አለማየኹ ለአሜርካ ድምጽ ተናግረዋል።
ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው ፌደራል ፖሊስ መምርያ ዛሬ ሄደው ጠይቀውት እንደነበር የገለጹት፣ ወይዘሮ ስንታየኹ፣ "እዚያ ከደረስን በኋላ የሆኑ ሰዎች፣ "እሱ እዚህ የለም” አሉን፡፡ ሌሎች ደግሞ እዛ እንደነበረ ነገሩን፡፡ በመጨረሻም፣ አግኝተነው ምግብ ሰጥተነው ጊቢውን ለቅቀን ወጣን። በኋላ አቶ ታዬ ራሱ ደውሎ መውጣቱን ነገረን፡፡ በቅርብ ለነበረ የቤተሰብ አባል ቶሎ እንዲሔድለት ነገርን። ከዛም ይዞት መጣ፣ ገና አሁን ነው ቤት የደረሱት" ብለዋል።
አቶ ታዬ ተመልሰው ለምን በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እስካኹን እንዳልነገሯቸው ወ/ሮ ስንታየው አክለው ተናግረዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የአቶ ታዬን ጉዳይ ሲከታተል መቆየቱን፣ በኮሚሽኑ የክትትልና የምርመራ ሪጅናል ዲሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ለአሜሪካ ድምጽ ገልጸዋል።
አቶ ታዬ ደንደአ ለፍርድ ቤት ባቀረቡዋቸው አቤቱታዎች ዙርያ፣ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኑ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የገለፁት ሰላማዊት ግርማይ፣ ምርመራው እንደተጠናቀቀም ውጤቱም ይፋ ይደረጋል ብለዋል። ባለፈው አመት፣ ታህሳስ ወር ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ድኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፣ በመጀመሪያ በሦስት ጉዳዮች ተከሰው ነበር፡፡ በሒደት ግን ሁለቱ ክሶች ውድቅ ተደርገው፣ በሦስተኛው ጉዳይ ማለትም “ህገወጥ የጦር መሳርያ ይዞ በመገኘት” በሚለው ክስ ታኅሳስ 3፣ 2017 ዓ.ም. በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የመከላከያ ምስክሮችን ለማሰማት ተቀጥረዋል፡፡
መድረክ / ፎረም