በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወላጆችንና መምህራንን ግራ ያጋባው የ2013 ትምህርት ዘመን


አቶ መላኩ ብርሃኑ ከልጆቻቸው ተማሪ ሴንፐር መላኩ እና ሚካኤል መላኩ ጋር
አቶ መላኩ ብርሃኑ ከልጆቻቸው ተማሪ ሴንፐር መላኩ እና ሚካኤል መላኩ ጋር

የትምህርት ሚኒስቴር የ 2013 ዓ.ም. ትምህርት ዘመንን ለማስጀመር ትምህርት ቤቶች ከ ነሐሴ 20 2012 ዓ.ም. ጀምረው ተማሪዎችን እንዲመዘግቡ ማዘዙን ተከትሎ፣ የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው። ላለፉት ስደስት ወራት ከጉዋደኞቻቸውና ከአስተማሪዎቻቸው ርቀው የከረሙ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስና ትምህርታቸውን ለመቀጠል ጉዋጉተው እይጠበቁ ቢሆንም፣ በሀግሪቱ የኮሮና ቫይረስ ተያዦች ቁጥር በየእለቱ እያሻቀበ በሄደበት ወቅት፣ አብዛኞች ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ለመወሰን መቸግራቸውን ይናገራሉ። በፈታኙ የኮሮና ወቅት የሚደረገውን የትምህርት አጀማመር አስመልክቶ ተማሪዎችን፣ ወላጆችንና መምህራንን አነጋግረናል።

የአስር አመቷ ህፃን ተማሪ ሴንፐር መላኩ የምትማርበት ቪዥን አካዳሚ ትምህርት ቤት ከስድስት ወር በፊት በኮሮና ምክንያት ሲዘጋ የ 4ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። ያለፉትን ስድስት ወራትም በቤት ውስጥ በማንበብ፣ ቴሌቭዥን በማየትና፣ ስእሎችን በመሳል ጊዜዋን አሳልፋለች። በአዲሱ የትምህርት ዘመን ግን ሴንፐር ትምህርት ቤት ተከፍቶ ጉዋደኞቿንና አስተማሪዎቿን ለማግኘት ጉዋጉታለች።

የሰንፔር አባት አቶ መላኩ ብርሃኑ ሴንፐርና ሁለተኛው የስድስት አመት ልጁ ሚካኤል፣ በኮሮና ምክንያት እቤት ውስጥ መዋላቸው ያሳደረባቸውን የስነ ልቦና ጫና በማስተዋሉ ትምህርት ቤት የሚመለሱበት ጊዜ እንደሚናፈቀው ይናገራል። በተለይ ደግሞ ሴንፐር ከትምህርትቤት መራቋ ያሳደረባትን ጭንቀት እንዲህ ይገልፀዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር፣ ካሳለፍነው አመት መገባደጃ ጀምሮ ለ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ምዝገባ እንዲጀመር መመሪያ በሰጠው መሰረት ትምህርት ቤቶች ምዝገባ እያካሄዱ ነው። አንድ አንድ የግል ትምህርት ቤቶችም የቀነ ገደብ አስቀምጠው በዛን ግዜ ውስጥ ያልተመዘገቡ ልጆች በቀሪው አመት ትምህርት ቤት መግባት እንደማይችሉ ለወላጆች ማስጠንቀቂያ እየላኩ ይገኛሉ።

ልጆቹን ገና ያላስመዘገበው መላኩ ግን የኮሮና ወረርሽኝ ቁጥሩ እየጨመረ ባለበት ሰዓት ልጆቹን ትምህርት ቤት ለመላክ ዝግጁ አይደለሁም ይላል።

ትምህርት የሚጀመርበት ቀን በይፋ ባይነገርም የትምህርት ሚኒስቴር የቀጣይ አመት የትምህርት ምዝገባ እንዲካሄድ ሲወስን፣ ትምህርት ቤቶችም በሀላፊነት አካላዊ ርቀትን ጠብቀው ለማስተማር የሚያስችላቸውን የንፅህና መጠበቂያዎችን ማዘጋጀት እንዲጀምሩ ምክር ሰጥቷል።

በቤተልሄም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ስንዱ ተፈራ ከትምህርት ቤት ርቃ የቆየችባቸው ጊዜያት ያሳስባታል። በዚህም ምክንያት ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን ጥንቃቄ ካደረጉ ተማሪዎች ማስክ በማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና እጅን ቶሎ ቶሎ በመታጠብ ትምህርታቸውን መቀጠል ይቻላሉ ትላለች።

ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ኮሮናን ለመከላከል ምን ማድረግ አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ትምህርት ሚኒስትር ከግምት ውስት ካስገባቸው አማራጮች መሃል ትምህርት በፈረቃ እንዲሆን ማድረግ ነው።

መላኩ ግን ንፅህና የመጠበቂያ መመሪያዎቹም ሆኑ ተማሪዎች በፈረቃ ይማሩ የሚሉት አማራጮች ተግባራዊነታቸው አጠራጣሪ ነው ይላል።

በትምህርት መጀመር ጉዳይ በወላጆች ዘንድ የሚታየውን ግራ መጋባት ከስራ ገበታቸው ርቀው የከረሙት መምህራንም ይጋሩታል። በአንድ ክፍል ውስጥ በአማካኝ ከ 40-50 ተማሪዎች ያስተምሩ እንደነበር የነገረን በቦሌ ህብረተሰብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህር የሆነው ሙሉጌታ ታያቸው፣ መምህራን ወደ ስራቸው መመለስ ቢፈልጉም፣ የጤናው ጉዳይም ያሳስባቸዋል ይላል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኃላ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከመጋቢት ሰባት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቢቆዩም በድህረገፆች፣ ቴሌቭዥንና ሬዲዮ አማካኝነት ትምህርት ለማስቀጠል ሙከራ ሲካሄድ ቆይቷል። ከስምንተኛና እና 12 ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወሳጆች ውጪም ተማሪዎች በግማሽ ዓመት ውጤታቸው ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲዛወሩ ተደርጓል። የስምንተኛም ሆነ የ12 ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና መቼ እንደሚካሄድ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ

ወላጆችንና መምህራንን ግራ ያጋባው የ2013 ትምህርት ዘመን
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:20 0:00


XS
SM
MD
LG