በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ ክልል የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪዎች በጎርፍ ተጠቃን ይላሉ፤ አስተዳደሩ ጉዳቱ መጠነኛ ነው ብሏል


የክረምቱ ዝናብ በኢትዮጵያ አይሏል
የክረምቱ ዝናብ በኢትዮጵያ አይሏል

በኦሮሚያ በህይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም

በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ጎርፍ መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በአካባቢው የሚገኝ የሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤት ክፉኛ በጎርፍ መመታቱን ቦሩ ሮባ የተባሉ የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ ለቮኦኤ ገልጸዋል።

“የደረሰው ጉዳት በጣም ከባድ ነው። ጉዲና ቱምሳ GTS የተባለ ሃይስኩል (ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) አለ። ያን ትምህርት ቤት እንዳለ ወስዶታል (ጎርፍ)” ብለዋል አቶ ቦሩ ሮባ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን መስተዳድር በበኩሉ መጠነኛ ጎርፍ በመተሃራ ከተማ አቅራቢያ እንደነበረና ያስከተልው ከፍተኛ ጉዳት እንደሌለ ለቪኦኤ አብራርቷል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብራሃም አዱላ ጉዳቱ መጠነኛ ነው ብለዋል።

“የፈንታሌ ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው መተሃራ አቅራቢያ በሰቃ ሀይቅ የሚባል የተፈጥሮ ሃይቅ አለ። በበጋው ወር ውስጥም አልፎ አልፎ ዝናብ ይዘንብ ስለነበረ፤ መጀመሪያ ካለው የውሃ ይዘቱ የጨመረበት ሁኔታ አለ፤” ብለዋል።

በመተሃራ የስኳር ፋብሪካና በግል የከብት ማደለቢያ አካባቢ የተወሰነ ጥፋት መድረሱንና የሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤት በጎርፍ መጥለቅለቁን የተናገሩት አቶ አብርሃም አዱላ፤ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል አከታትሎ የጣለው ዝናብ በአምስት ወረዳዎች 37 ሰዎችን ሲገድል ከ6ሽህ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉን የክልሉ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የአስቸኳይ ጊዜ ሰራተኞች የተጎጂዎቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል በመግለጽ ላይ ናቸው።

የክረምቱ ዝናብ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ድርጅት አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG