በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን «አሁንም እየተዋከቡ ነው፤» ሲሉ፥ ተቃዋሚዎች ከሰሱ።


የአዲስ አበባ ምርጫ ተሳታፊዎች
የአዲስ አበባ ምርጫ ተሳታፊዎች

ምርጫው ተጠናቅቆ የኢህአዴግ አሸናፊነት ይፋ ከተደረገ ሁለት ሳምንታት በኋላ አንዲት የምርጫ ታዛቢ መገደላቸውን መኢአድ ሲያስታውቅ፤ በአባሎቹ ላይ የደረሰ ያለው ወከባና እንግልት የኦሮሞ ህዝብ ኮንግሬስ አመለከተ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ከተጠናቀቀና የቅድሚያ ውጤቶቹ ከተሰሙ ሁለት ሳምንታት ቢገባደዱም ከምርጫው ጋር ተያይዘው የሚነሱት ውዝግቦች ግን ዛሬም አላበቁም።

«የምርጫ ታዛቢ ሆነው ባቀረቡት ትችት የአንድ አባሌ ባለቤት ተገደሉ፤» ሲል፥ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ መኢአድ አስታውቋል።

በደቡብ ክልል የደራሼ ልዩ ዞን ሰብሳቢው የአቶ ገልገሎ ኮይታ ባለቤት፥ ወ/ሮ አማረች ገላኔ ባለፈው ዕሁድ በአንድ የመንግስት ታጣቂ መገደላቸውንና በጊዜው አብረዋቸው የነበሩ ሁለት ህፃናት ልጆቻቸውም ቆስለው በህክምና በመረዳት ላይ መሆናቸውን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ገልጠዋል።

በሌሎች አካባቢዎችም ደጋፊዎቻችንና አባሎቻችን በመንግስት የሚቀርቡ አገልግሎቶችን እየተነፈጉ ነው፥ ከማኅበራዊ ህይወትም እየተገለሉ ነው፤ ያሉት አቶ ማሙሸት አክለውም፤ «ይህ እየተፈፀመ ያለው ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑ በሠላማዊ መንገድ የሚደረገውን ትግል ይበልጥ አዳጋች አድርጎታል፤» ብለዋል።

የኦሮሞ ኅዝብ ኮንግሬስም በበኩሉ «በደጋፊዎቼ ላይ የሚደርሰው ወከባ አሁንም ቀጥሏል፤» ብሏል።

ከምርጫው በፊትና በምርጫው ዕለት የታሰሩ አብዛኞቹ አባላቱና ደጋፊዎቹ ቢለቀቁም «እየደረሰ ነው፤» ያለው ወከባ ግን፥ አሁንም አለማቆሙን ሊቀ መንበሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና ተናግረዋል።

መኢአድም ሆነ የኦሮሞ ኅዝብ ኮንግሬስ ላቀረቧቸው ክሶች ለጊዜው ማስተባበያ የሰጠ ወገን የለም።

XS
SM
MD
LG