በኬንያ ሊደረግ የታቀደውን የታክስ ጭማሪ በመቃወም ከተደረገው የወጣቶች ሰልፍ ጋራ በተያያዘ አንድ ሰው ተገድሏል፡፡
ፖሊሶችን የሚከታተለው ገለልተኛ ቡድን፣ ትላንት ኀሙስ የተካሔደውን ተቃውሞ ተከትሎ በናይሮቢ ሕይወቱ ያለፈው ግለሰብ፣ በፖሊስ ጥይት ተመትቶ እንደኾን እያጣራኹ ነው፤ ብሏል።
ፖሊስ፣ ዛሬ ዐርብ እንዳስታወቀው፣ ተቃዋሚዎቹ በሚቀጥለው ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሔድ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል፡፡
በኬንያ ወጣቶች መሪነት የተነሣሣውና ባለፈው ማክሰኞ በናይሮቢ ተጀምሮ በመላ አገሪቱ የተሰራጨው ተቃውሞ፣ በመጭው ማክሰኞ እ.ኤ.አ ሰኔ 25 ቀን ብሔራዊ የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ተቃዋሚዎች፣ በፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደስተኛ አለመኾናቸውን ሲገልጹ፣ ለብዙ ኬንያውያን ኑሯቸውን አስቸጋሪ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
የትላንቱ ሰልፍ በአብዛኛው ሰላማዊ የነበረ ቢኾንም፣ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ እና ውኃ በመርጨት በምክር ቤቱ አካባቢ የነበሩ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ሙከራ ማድረጉ ተነግሯል፡፡
ገለልተኛ ነው የተባለው የፖሊሶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን(IPOA)፣ በተቃውሞ ስፍራ ተገድሏል፤ የተባለው የ29 ዓመቱን ወጣት እና የተጠርጣሪውን ፖሊስ ጉዳይ እየመረመረ መኾኑ ተመላክቷል፡፡
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኬንያ ወኪል፣ ግለሰቡ ከፖሊስ ለመሸሽ ሲል በጥይት መመታቱን ሲገልጽ፣ የዐይን እማኞችም፣ ፖሊስ ተኩስ መክፈቱን መመልከታቸው ተናግረዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች ድርጅቶች፣ በናይሮቢ፣ ቢያንስ 200 ሰዎች መቁሰላቸውንና ከእነዚህም ስምንቱ ክፉኛ መጎዳታቸውን፣ የኬንያ ቀይ መስቀል አስታውቋል፡፡
መንግሥት፣ ለአንዳንድ የታክስ ጭማሬ ጥያቄዎች ምላሽ ቢሰጥም፣ ያጋጠመውን የበጀት እጥረት ለመፍታት፣ የነዳጅ ዋጋን ለመጨመርና የወጪ ንግድ ታክስን ከፍ ለማድረግ ዐቅዷል።
መድረክ / ፎረም