በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኒው ዮርክ ከተማ ባቡር ጣቢያ የደረሰው ጥቃት

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊሶች ትናንት በከተማዋ ብሩክሊን ቀበሌ በሚገኝ የከተማ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ጢስ የሚያንቦለቡል ፈንጂ ካፈነዳ በኋላ ተኩስ ከፍቶ አስር ሰው ያቆሰለው ለመያዝ እየሞከሩ ናቸው።

ፖሊሶች ከጥቃቱ ጋር ግንኙነት እንዳለው የተጠረጠረውን መኪና የተከራየ እሱ ነው የተባለውን ፍራንክ ጄምስ የሚባል ሰው እየፈለጉ ናቸው።

ፖሊሶች መኪናውን ጥቃቱ ትናንት ጠዋት ከደረሰበት ስፍራ ማታ ላይ አስነስተውታል። ጥቃቱን ያደረሰው እሱ ይሁን አይሁን ግን አላረጋገጥንም በማለት ፖሊስ አጥብቆ አስታውቋል። የኒው ዮርክ ፖሊስ የደህንነት ክፍል ሹሙ ከፊላዴልፊያ ከተማ የዕቃ ማጓጓዣ ዩ ሆል መኪናውን የተከራየው ፍራንክ ኢ ጄምስ የተባለ የስድሳ ሁለት ዓመት ሰው ነው ብለን እናምናለን፤ ግለሰቡ የዊስከንሰን እና የፊላዴልፊያ የድሮ አድራሻ አለው፤ ከትናንቱ ጥቃት ጋር ግንኙነት ይኖረው እንደሆነ ልናነጋግረው እየፈለግነው ነን። ጥቃቱን ያደረሰውን ወይም መኪናውን የተከራየውን ሰው የሚያውቅ ሰው ካለ መረጃ እንዲሰጠን እንጠይቃለን ብለዋል።

ባለሥልጣናት የተፈላጊውን የጀምስን የማኅበራዊ መገናኛ እንቅስቃሴ ፖሊስ እየተከታተለ ሲሆን በአንዳንዱ ይዘት የተነሳ ለኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኢሪክ አደምስ የተጠናከረ ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል። ከንቲባው ኮሮናቫይረስ ይዟቸው ራሳቸውን ለይተው ተቀምጠዋል።

በጥይት ከተመቱት ሰዎች መካከል አምስቱ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ቢሆኑም ለህልፈት ግን ያደርሳቸዋል የሚል ሥጋት እንደሌለ ነው የተገለጸው። ቀደም ሲል ባለሥልጣናቱ በሰጡዋቸው መግለጫዎች ጥቃቱን በአሸባሪ ድርጊትነት እንዳልተፈረጀ አስታውቀዋል።

ፖሊሶች ጥቃቱ ከተፈጸመበት ሥፍራ ሽጉጥ ጥይቶች የጢስ ፈንጂ እና የመኪናዋን ቁልፍ ይዘዋል።


XS
SM
MD
LG