በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኒጄር ወታደሮች ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን ማስወገዳቸውን አስታወቁ


በኒጄር ያመፁ ወታደሮች፣ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን እንዳስወገዷቸው፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን አስታውቀዋል።
በኒጄር ያመፁ ወታደሮች፣ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን እንዳስወገዷቸው፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን አስታውቀዋል።

በኒጄር ያመፁ ወታደሮች፣ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን እንዳስወገዷቸው፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን አስታውቀዋል። የአገሪቱን ድንበር እና የመንግሥትን ተቋማት ለጊዜው ሲዘጉ፣ የሰዓት እላፊ ገደብም ጥለዋል።

ኮሎኔል-ሜጀር አማዱ አብድራሜ፣ በሌሎች ዘጠኝ ወታደሮች ታጅበው፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው፥ “እኛ የመከላከያ እና የጸጥታ ኃይሎች፥ የፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙም አገዛዝን አስወግደናል፤” ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ባዙም፣ ዛሬ ኀሙስ ማለዳ፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዴሞክራሲያዊ ትግል ያገኙትን ድል እንደሚያስጠብቁ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ባዙም እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሃሱሚ ማሱዱ፣ የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች፣ በመካሔድ ላይ ያለውን ሥልጣን ነጠቃ እንዲቃወሙ ጥሪ አድርገዋል።

ምዕራባውያን ባለሥልጣናት፣ የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የደረሰበትን ደረጃ በግልጽ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ አገራቸው፣ ከፕሬዚዳንት ባዙም ጎን እንደኾነችና እንደምትደግፋቸው ትላንት አስታውቀዋል። ትላንት በስልክ አግኝተው እንዳነጋገሯቸውም ገልጸዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር አዛሊ አሱማኒ፣ በኒጄር እየኾነ ያለውን አውግዘው፣ ፕሬዚዳንት ባዙም እና ቤተሰባቸው እንዲለቀቁ ጥሪ አድርገዋል።

የኒጄር ወታደራዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ፣ ወታደሮቹ የወሰዱትን ርምጃ በመደገፍ፣ የፕሬዚዳንት ባዙም እና የቤተሰባቸው ደኅንነት ግን እንዲጠበቅ ጥሪ አድርገዋል። የአገሪቱ ጦር አዛዥም፣ የሥልጣን ነጠቃ ሙከራ በማድረግ ላይ ያሉትን ወታደሮች እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

በኒጄር ትላንት፣ ፕሬዚዳንታዊ የጥበቃ ኃይሉ፣ ፕሬዚዳንቱን ከቤተ መንግሥቱ እንዳይንቀሳቀሱ በማገድ፣ ቤተ መንግሥቱን ከሌላው የከተማው ክፍል የሚያገናኘውን መንገድ ዘግተዋል።

ኒጄር ከፈረንሳይ፣ እ.አ.አ በ1960 ነፃነቷን ከተቀዳጀች ወዲህ፣ አራት የተሳኩ መፈንቅለ መንግሥቶችንና በርካታ የመፈቅለ መንግሥት ሙከራዎችን አስተናግዳለች፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG