በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መፈንቅለ መንግሥት በበዛባት ኒጀር የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ እና ጽ/ቤት በልዩ ጥበቃቸው ተዘጋ


ፎቶ ፋይል፦ የኒጀር ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም
ፎቶ ፋይል፦ የኒጀር ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም

የመንግሥት ግልበጣ በተደጋጋሚ በሚያውካት ኒጀር፣ የወቅቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙም መኖሪያ ቤት እና ጽ/ቤት፣ ዛሬ ረቡዕ፣ በልዩ ጥበቃ አባሎቻቸው እንደተዘጋ ተነገረ፡፡የፕሬዚዳንቱን የቅርብ ምንጮች ጠቅሶ ኤኤፍፒ እንደዘገበው፣ ምክንያቱ ግልጽ አልተደረገም፡፡

በኒያሜ የሚገኘው የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ እና ጽ/ቤት ዝግ ቢኾንም፣ በአካባቢው ያልተለመደ ወታደራዊ ስምሪት ወይም የተኩስ ድምፅ እንዳልተሰማ፣ መደበኛው የትራፊክ እንቅስቃሴም እንዳልተስተጓጎለ፣ የኤኤፍፒ ዘጋቢ ተመልክቷል፡፡

ኒጀር፣ እ.ኤ.አ. በ1960 ከፈረንሳይ ነፃ ከወጣች በኋላ፣ ቢያንስ አራት የመንግሥት ግልበጣዎችና ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎችን አስተናግዳለች። የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር፣ መረጋጋት አብዝቶ ከራቃቸው የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ እንደኾነች ተዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዚዳንት ባዙም፣ የፈረንሳይ ወዳጅነታቸው ይነገርላቸዋል፡፡በአገሪቱ፣ የመጨረሻው መፈንቅለ መንግሥት የተካሔደው፣ እ.ኤ.አ በ2010 ሲኾን፣ በጊዜው ፕሬዚዳንት የነበሩት መሐመዱ ታንድጃ ከሥልጣን ተወግደዋል፡፡

ይኹን እንጂ፣ እ.ኤ.አ. መጋቢት 31 ቀን 2021፣ ባዙም ቃለ መሐለ ከሚፈጽሙበት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የተደረገ ሙከራ እንደነበር፣ በወቅቱ የደኅንነት ምንጭ ተገልጿል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG