በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቄለም ወለጋ የተገደሉ ሰዎችን አስክሬን በመቅበር ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ


የኢትዮጵያ ካርታ
የኢትዮጵያ ካርታ

በኦሮምያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ ሃዋ ገላን ወረዳ ውስጥ “መንደር 20” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “ሸኔ” ብለው በጠሩት ታጣቂዎች መገደላቸውን የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራችው የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ።

በኦሮምያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ ውስጥ መንደ ር 20 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትናንት ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ረፋዱ 4፡00 ሰዓት ድረስ፤ መንግሥቱ በሽብር የፈረጀውና ባለሥልጣናቱ “ሸኔ” እያሉ የሚጠሩት፤ “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” እንደሚባል የሚናገረው ታጣቂ ቡድን በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ጭፍጨፋ ማካሄዱን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደሉን አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለትም የሟቾችን አስክሬን እየሰበሰቡ ሲቀብሩ መዋላቸውን፤ ቁጥራቸውን መግለፅ ያልቻሏቸው ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ገልፀዋል። “እኔም አምስት ቤተሰብ ቀብሬያለሁ። ሁሉንም በአንድ ጉድጓድ ነው የቀበርኳቸው” ብለዋል።

ግድያው የተፈፀመው በጅምላ በመሆኑ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ወጥተው አስክሬን እንዲቀብሩ በድምፅ ማጉያ ጥሪ ሲደረግ መዋሉን የተናገሩት እኚህ ግለሰብ፤ “በጣም ብዙ ሰው ነው የሞተው። ዛሬ ስንቀብር ውለን እኛ ደክሞን ተመለስን። አሁንም ግን በድምፅ ማጉያ ውጡና ቅበሩ እየተባለ እየተነገረ ሰዉ ሊቀብር እየወጣ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “በኦሮምያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈፅሞባቸዋል" ሲሉ ትላንት ማምሻውን በማኅበራዊ ትስስር ለግድያው ሸኔን ተጠያቂ ሲያደርጉ፤ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ ደግሞ ለግድያው የመንግሥትን ታጣቂ ሚሊሺያዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

ጥቃቱ ከተፈፀመበት መንደር 20 በ10 ኪ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው መንደር 17 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሚኖሩ የተናገሩት ሌላው ነዋሪ፤ ጥቃቱ መፈፀሙን እንደሰሙ ወደ ቦታው በመሄድ ሁኔታውን ከተጎጂዎች መስማታቸውን ገልፀዋል። በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን እና ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዋቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት የመንግሥት ታጣቂዎች አካባቢውን እንደተቆጣጠሩ የሚናገሩት እኚሁ ግለሰብ እርሳቸው የሚኖሩበትና በቅርብ ርቀት የሚገኘው መንደር 17 ተብሎ የሚጠራው አካበቢ ነዋሪዎች ከፍተኛ ሥጋት ላይ በመሆናቸው ቤታቸውን ለቀው በመውጣት መንገድ ዳር ተቀምጠው መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጥቃቱ “ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል” ሲሉ ትናንት ማምሻውን በማኅበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ላይ ባወጡት ፅሁፍ አስታውቀዋል።

"በኦሮምያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈፅሞባቸዋል" ለግድያው ሸኔን ተጠያቂ ሲያደርጉ፤ “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” እንደሚባል የሚናገረው ታጣቂ ቡድን ደግሞ መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል። ዘውግን መሰረት ባደረገውና ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተባባሰው ጥቃት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ ተገድለዋል።

ትናንት ሰኞ ከአዲስ አበባ 400 ኪሜ ላይ በምትገኘው ቄለም ወለጋ ዞን በሚገኙ ሁለት መንደሮች ውስጥ ጥቃት መፈጸሙን በመንግሥት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል። ኮሚሽኑ አክሎም ተደጋጋሚ ጥቃት በተፈጸመበት የኦሮምያ ክልል መንግሥት ተጨማሪ ኃይል እንዲልክ ጠይቋል።

ትናንት ሰኞ ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ በዋናነት የአማራ ተወላጆች የሚኖሩበት አንደሆነ ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለግድያው ሸኔ ብለው የጠሩትን እና በአሸባሪነት የተፈረጀውን ቡድን ተጠያቂ ሲያደርጉ፤ “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” እንደሚባል የሚናገረው ታጣቂ ቡድን ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ታርቢ ደግሞ ለግድያው የመንግሥትን ታጣቂ ሚሊሺያዎችን ተጠያቂ አድርገው፣ በመንግሥት ወደ አካባቢው የተላከው ሰራዊት ግድያውን ለማስቆም ምንም ያደረገው ነገር የለም ብለዋል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሁለት ዲቪዥኖችና ሌሎች አጋር ኃይሎች ማቻራን ጨምሮ የቄለም ወለጋ ከተማን ተቆጣጥረዋል። የአገዛዙ ሚሊሽያ በጅምላ ግድያ ሲፈጽም ግን ለማስቆም አልሞከሩም። አገዛዙ ጣት ስለጠቆመ ከተጠያቂነት የሚያመልጥ ይመስለዋል” ሲሉ ኦዳ ታርቢ ትናንት በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

“ሀገር በቀልም ሆነ ዓለም አቀፍ አካላት ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድና ዐቢይና ተባባሪዎቹን ለጭካኔያቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ መጠየቅ ይኖርባቸዋል” ሲሉም አክለዋል።

በአሜሪካ የሚገኘው የአማራ ማኅበር ጥቃቱ ከተፈጸመበት ቦታ አገኘሁ ባለው መረጃ ከ150 እስከ 160 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ትናንት ለአሶስዬትድ ፕሬስ ዜና ወኪል ገልጿል። “የአማራ ተወላጆች በጥቃቱ ኢላማ ተደርገዋል” ሲል ማኅበሩ አስታውቋል። ከግድያው የተረፈን ግለሰብ ጠቅሶ “የሟቾቾ ቁጥር ቢያንስ 300 ነው” ሲል የአማራ ሚዲያ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

“የፀጥታ አካላት ከሚያደርሱበት ዱላ የፈረጠጠው የሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋ በዜጎች ላይ አደጋ እያደረሰ በመሸሽ ላይ ነው። በኦሮምያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ሰኞ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ቢያሳውቁም፣ ምን ያህል ዜጎች እንደተገደሉ ግን ያሉት ነገር የለም።

“በዜጎቻችን ላይ በደረሰው መከራ እያዘንን ይሄንን አሸባሪ ቡድን እስከመጨረሻው ተከታትለን ከህዝባችን ጋር እናስወግደዋለን” ሲሉም አጭር መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።

የትናንቱ በቄለም ወለጋ የተፈጸመው ግድያ ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ከሁለት ሳምንት በፊት በእዛው አካባቢ ምዕራብ ወለጋ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ መገደላቸውን ተከትሎ የተፈጸመ ነው። በቶሌው ግድያ 338 ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር። ሌሎች ወገኖች ቁጥሩን ከዚህ ከፍ ያደርጉታል። የአሶስዬትድ ፕሬስ ዜና ወኪል የአካባቢ ምንጮችን ጠቅሶ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በወቅቱ ዘግቧል። በዚህም ግድያ መንግሥት ሸኔ ያለውን ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ ሲያደርግ፥ ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ የመንግሥት ሚሊሻዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።

/ዘገባው የአስቴር ምስጋናው ነው። የአሶስዬትድ ፕሬስ፣ ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ ዘገባዎች ታክለውበታል/

please wait

No media source currently available

0:00 0:08:51 0:00

XS
SM
MD
LG